፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 28 2016| NBC ETHIOPIA-ይህ የአፍሪካዊያንን አንገት ያስደፋ ፤ጠባሳው ዛሬም ድረስ ጨርሶ ያልሻረ የጨለማው ዘመን የወለደው የሲቃ ድምጽ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ አፍሪካዊ ሆኖ መፈጠር ሃጥያት፣ስቃይ እና መከራ ነው፡፡በነጮቹ ዘንድ ከአፍሪካዊያን በተሻለ የቤት የተከበረ ነበረ፡፡ክቡሩ የሰው ልጅ እንደ ሙክት በግ ተሰልፎ ጨረታ የተደረገበት አሰቃቂ ዘመን ይሄኛው ለጉልበት ስራ ይሆናል!እቺኛዋ አርጅታለች፣ እየተባለ የሰው ልጅ እንደ ሸቀጥ የተቸበቸበበትና አትላንቲክ ባህርን ያቋረጥበት ታሪክ በማህደሩ የከተበው አሳፋሪ ክስተት ነው፡፡ ይህ ሁሉ በደል በሚፈፀምበት የጨለማ ወቅት ለብዙዎች ብርሃንን የፈነጠቀች አንዲት ሴት ተፈጠረች Harriet Tubman (ሄርየት ታብማን)”!
የተወለደችው እ.ኤ.አ በ 1822 በአሜሪካዋ “Maryland” ነው። ቤተሰቦቿ ባርያዎች ሲሆኑ ነጮቹ ገና በ 12 ዓመቷ የጥጥ እርሻ ውስጥ ቀኑን ሙሉ ጥጥ ሲያስለቅሟት ይውሉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በአንዱ ባርያ የተበሳጨ ነጭ የወረወረው ከባድ ብረት ጭንቅላቷን መቷት ዕድሜ ልኳን ለከባድ ህመም እንድትጋለጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
በወቅቱ በባሪያዎች በተለይም በሴት ባሪያዎች ላይ ይደርሱ የነበሩ በደሎች እጥፍ የደርሰባት ሄርየት እድሜዬን በሙሉ እንስሳ ሆኜ አልኖርም ብላ በመወሰን እ.ኤ.አ በ1849 ወደ “Philadelphia” ጠፋች። የጠፋችው ግን ለማምለጥ ሳይሆን በህይወቷ ፈርዳ በባርነት የሚሰቃዩ ወገኖቿን ለማስመለጥ ነበር።

ሄርየት ከ 1850 ጀምሮ ለተከታታይ አስራ ሶስት አመታት በድብቅ አሳቻ ሰዓቶችን እየጠበቀች ባርያ ሆና ትኖርበት ወደ ነበረው ቦታ በማምራት ከ 700 በላይ ባርያዎችን ማስመለጥ የቻለች የክፍለ ዘመኑ የነጻነት ፋና ወጊ ለመሆን በቃች፡፡እጅግ የሚደንቀው ባርያዎቹን በምታስመልጥበት ወቅት አንዳንዶቹ ፈራ ተባ እያሉ አናመልጥም እያሉ ሲያስቸግሯት ግንባራቸው ላይ “Revolver” ጥይት ደቅና ወደኃላ እንዳይመለሱ ታስፈራራቸው ጭምር ነበር።
ነጻ የወጡትንና በባርነት ሲማቅቁ የነበሩትን ወደ ሌላ ግዛቶች ወስዳ ስራ እንዲሰሩ እና እንዲቋቋሙም ማድረግ ችላለች፡፡ ይቺህ ጀግና ሴት የመፅሃፍ ቅዱሱ ሙሴ በግብፅ ባርነት የተያዙትን እስራኤላዊያንን ባህር ከፍሎ ወደ ቃል ኪዳኗ ምድር ከወሰደበት ታሪክ የማይተናነስ ተግባርን በመፈፀሟ “ሴቷ ሙሴ” የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቷት ነበር። “Harriet Tubman” ካስመለጠቻቸው ባርያዎች ውስጥ አንዱም አለመያዙ ታሪክ በማህደሩ ከትቦ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡
“Harriet Tubman” ለሰራችው ስራ የተሰጣት የተለየ ገንዘብም ሆነ ስጦታ የለም! በመጨረሻም እጅግ በቆረቆዘ ደህንነት ውስጥ ኖራ በ 90 ዓመቷ እ.ኤ.አ 1913 ላይ አርፋለች!

ዛሬ ላይ “Harriet Tubman” ለከወነችው ድንቅ ተግባር መታሰብያነት ብዙ አደባባዮች እና ቤተ መፅሃፍቶች በስሟ ተሰይመዋል። ሃውልቶች ቆመውላታል። በታሪክም “ባርነትን ለማስወገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ዋና ዋና ግለሰቦች” መካከል አንዷ ሆና ሰፍራለች!
እ.ኤ.አ 2016 ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት “Barack Obama” የአሜሪካ 20 ዶላር ላይ ያለው 7ተኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበረው “Andrew Jackson”ተነስቶ የ “Harriet Tubman” ፎቶ ሃገሪቱ 20 ዶላር ኖት ላይ እንዲታተም ውሳኔ አስተላልፎ ነበር! ነገር ግን ሂደቱ ሳይቋጭ “Obama” ስልጣን በመልቀቁ ይህ ውጥን በዕቅድ ቀርቷል፡፡
በ-ፀጋሁን አሰፋ












