፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 27 2016| NBC ETHIOPIA-11ኛው አለም አቀፍ የድራም እና የባህል ፌስቲቫል ከአለም ዙሪያ የተወጣቱ 40 የሚሆኑ ባህላዊ ቡድኖችን በማሳተፍ በታሪካዊቷ ካይሮ ተጀምሯል።
በዚህ አለም አቀፍ ሁነት ከ30 በላይ ቡድኖ የተሳተፉ ሲሆን፣ ከፍልስጤም ፣ከጃፓን፣ ከቻይና እንዲሁም ከህንድ እና ከሌሎች ሀገራት የተሰባሰቡ የባህል ቡድኖችን አሳትፏል ፌስቲቫሉ።
የካይሮ የድራም ፌስቲቫል በግብፅ ካይሮ የሚካሄድ ዓመታዊ ዝግጅት ነው። ጅማሮውን ያደረገው እ.ኤ.አ በ2009 ሲሆን በመንፈሳዊ ዜማ የሰላም መልዕክት የማስተላለፍ ዓላማን ያነገበ ነው።
ፌስቲቫሉ “ፍቅርን፣ ብሩህ ተስፋን እና መቻቻልን በመስበክ የሰላምን መልዕክት ለአለም ለማድረስ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል። ዘንድሮም በዓሉ ዓመታትን ተሻግሮ ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል።
በአለም አቀፍ እና በታዋቂ የግብጽ ሙዚቀኞች በሚቀርቡ የሙዚቃ ትርኢቶች ደምቆና አሸብርቆ ይከናወናል። በየዓመቱ በካይሮ በተለያዩ መድረኮች ፣የህዝብ ቦታዎች፣ የኮንሰርት አዳራሾች እና የባህል ማዕከሎች ውስጥ በድምቀት ሲካሄድ የቆየ ልዩ ክብረ በዓልም ነው።

የፈስቲቫሉ ተሳታፈዎች የተለያዩ ሀገራት ባህሎች እንዲሁም ባሕላዊ ዜማዎችን፣ የተለያዩ የከበሮ አጨዋወት ዘይቤዎች የመማር እና የመሞከር እድሎችን ያገኛሉ። የካይሮ የድራም ክብረ በዓል ከግብፅ እና ከአለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ የሙዚቃ አድናቂዎችን በየዓመቱ ያሰባስባል።
የዘንድሮም ፌስቲቫል ‘’ ከበሮ ለሰላም ውይይት” በሚል መሪ ቃል ከብዙ ሀገራት የተውጣጡ የጥበብ ቡድኖች የሙዚቃ ስራቸውን እንዲያካፍሉ፣ የባህል ውይይት እንዲያበረታቱ እና ሰላምና መደመርን በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲቀበሉ ጥሪ ያቀረበ ነው ተብሏል።
ከየሀገሩ የተወጣቱ የባህል ቡድኖች በቀለማት አሸብርቀው በድምቀት ባሕላዊ የዳንስ ጭፈራዎች፣ድራማዊ ሙዚቃዎች እና ዘፈኖችን አቅርበዋል።
በፌስቲቫሉ ከ15,000 በላይ የሙዚቃ አድናቂዎች እና የከበሮ ተጫዋቾች መገኘታቸውን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።
የፌስቲቫሉ መስራች እና ዳይሬክተር ኢንቲሳር አብደል ፈታህ “ፍቅርን፣ ይቅርታን እና ሰላምን ለማጉላት ከአለም ባህሎች ጋር ለመተዋወቅ የምንችለውን ያህል እየሞከርን ነው ሲሉም ተናገረዋል።
የፍልስጤም የፋሎጃ የባህላዊ ጥበባት ቡድን መሪ ራፊቅ አል-ታዊል ፌስቲቫሉ ባህላዊ ጥበቦችን በመቀበል እና በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ፣መንፈሳዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ እንደ አንድ ልዩ መድረክ ነው የሚያገለግለው ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት 6 አመታት ቡድናቸው በፌስቲቫሉ ላይ መሳተፋቸውን ገልፀው ዝግጅቱ የፍልስጤም ባህላዊ ጥበባትን ለመላው አለም ለማሳየት ምቹ መድረክ ነውም ብለዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የታደመችው ማናል ካማል እንዲህ ስትል የተሰማትን ትናገራለች። ግብፅ እንደዚህ አይነት ዝግጅት በማዘጋጀቷ ከአለም ዙሪያ ካሉ ሀገራት ባህሎችን እንናውቅ እና እንድንዝናና በማድረግ መልካም እድልን አግኝተናል።
በ-ሀይማኖት ወርቁ












