፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 27 2016| NBC ETHIOPIA-ለበርካታ የአለም ሀገራት የራስ ምታት ሆኖ የቆየው የአየር ንብረት ለውጥ አሁንም በዜጎች እና በካባቢ ላይ ውስብስብ የተፈጥሮ ሚዛን መዛባትን እያስከተለ ቀጥሏል ፡፡
የአየርንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ደግሞ ለሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች መንስኤ እንደሆነ ይነገራል ፡፡ ከ2000 እስከ 2019 ባለው ግዜ ውስጥ በየ አመቱ 489 ሺ በላይ ሰዎች ከከፍተኛ ሙቀት ጋር በተገናኘ ህይወታቸውን እንዳጡ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
በአውሮፓም በ2022 70ሺ ሰዎች ከከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ ለህልፈት ተዳርገዋል ፡፡
በአሁኑ ሰዓትም በህንድ ከከፍተኛ ሙቀት ጋር በተገናኘ በሶስት ቀናት ውስጥ ከ 50 ሰዎች በላይ ህይወታቸውን ማጣታቸው ተገልጿል፡፡

በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በምዕራብ ህንድ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከ45-46 ዲግሪ ሴልሽየስ ከፍተኛ ሙቀት ተመዝግቧል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 50 ዲግሪ ሴልሽየስ ከፍ ማለቱን መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡
አብዛኛው ሞት የተመዘገበውም ሀገሪቱ በአለም ላይ ግዙፉን የፖለቲካ ምርጫ በምታካሄድበት በመጨረሻው ቀን ላይ ነው ፡፡
በሰሜናዊቷ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በሳምንቱ መጨረሻ በሙቀት ሳቢያ 33 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በኦዲሻ ግዛት ደግሞ 20 የሚጠጉ ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን አንድ የሀገሪቱን ባለስልጣን ዋቢ አደርጎ ቢቢሲ ዘግቧል።በአንዳንድ አካባቢዎችም አደገኛና አስፈሪ የሙቀት መጠን መመዝገቡን ቀጥሏል ነው የተባለው።
በህንዷ ባሊኣ ቅዳሜ የሙቀት መጠኑ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ወደ 61 ዲግሪ ሴልሽየስ ከፍ ማለቱን እና በመላው ሀገሪቱ የ58 ሰዎች ህይወት ማለፉን የህንድ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ከሟቾቹም ውስጥ በስራ ላይ የነበሩ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ አንዳንድ ለምርጫ ተሰልፈው የነበሩ መራጮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ህንድ በየአምስት አመቱ በበጋ ወር ምርጫ የምታካሂድ የነበረ ቢሆንም በዘንድሮ አመት የተከሰተው ከፍተኛ መጠን ያለው እና ለበርካታ ቀናት የቆየው ሙቀት ተግዳሮት ሆኖባት ሰንብቷል ፡፡

ህንድ ለከፍተኛ ሙቀት እንግዳ ባትሆነም የአሁኑ ግን ከሌላው ግዜ ከፍ ያለ እና ረዘም ላለ ቀን የቆየ ነው ፡፡ በርካታ ዜጎችም ለውሃ እና መብራት እጦት ተዳርገዋል ፡፡
በሙቀቱ ምክንያትም በ2021 በህንድ ከ167 ቢሊዮን በላይ የስራ ሰአት መቃጠሉን አዲሰ የውጣ ጥናት ያሳያል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከአጠቃላይ ምርት ከምታገኘው ገቢ 5.4 በመቶ የሚሆነውን እንድታጣ ዳርጓታል ፡፡
በመላው እስያ የሚገኙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከከፍተኛ ሙቀት ጋር እየታገሉ እንደሆነ የዘርፉ ባለሞያዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ጎረቤትዋ ፓኪስታንም ባለፈው ሳምንት ከ 52 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ የሙቀት መጠንን ማስመዘግቧ እንዲሁም ሙቀቱ እየጨመረ በመምጣቱ የደን ቃጠሎ መከሰቱ ይታወሳል፡፡
በሀገረ አሜሪካም በሳለፍነው አመት ከ2600 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ብክለትን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ቻይና፣አሜሪካ እና ህንድ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ ፡፡
በ- የአብስራ ብርሃኑ












