፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 26 2016| NBC ETHIOPIA-አለም አቀፍ ተቀባይነትን ባተረፉ ፊልም ጸሀፊያን የሚጻፉ እና ታዋቂ ተዋንያኖች የሚሳተፉባቸው ፊልሞች ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ እና በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው ፡፡
ለፊልም አፍቃሪያን በመጪው የፈረንጆቹ ሰኔ ወር ለእይታ የበቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ የባህር ማዶ ፊልሞች ልንነግራችሁ ወደድን፡፡
ባድ ቦይስ ራይድ ኦር ዳይ( Bad Boys Ride or Die)

የበርካቶች አድናቆት ተችሮታል እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 1995 ታዋቂዎችን ተዋናዮች አጣምሮ ለእይታ የበቃው… ባድ ቦይስ የተሰኘው የምርመራ የአክሽን ኮሜዲ ፊልም፡፡ የሆሊዉድ ፈርጦቹን ዊል ስሚዝ እና ማርቲን ላውረንስን አጣምሮ ከዚ ቀደም ለተመልካች በደረሱት ባድ ቦይስ 1 ፣ ባድ ቦይስ 2 እንዲሁም በ 2020 በተለቀቀው ባድ ቦይስ ፎር ላይፍ በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ተመልካቾችን ማግኘት ችሏል፡፡
በመጪው ሰኔ ወር ደግሞ ባድ ቦይስ ራይድ ኦር ዳይ የተሰኘ አራተኛ ከፍሉን ለተመልካቾን እንደሚያደርስ ይጠበቃል ፡፡ በታዋቂዎች Adil El Arbi እና Bilall Fallah ዳይሬክት የተደረገው ፊልሙ ቢቢሲ ባወጣው በሰኔ ወር ሊታዩ የሚገባቸው ምርጥ ፊልሞች ዝርዘር ውስጥ ተካቷል፡፡
ፊልሙም መርማሪዎቹ ማይክ ሎሬይ እና ማርከስ በርኔት በህይወት የሌሉት ካፒቴን ኮንራድ ሃዋርድ ከሮማኒያ ማፊያ ጋር ተሳትፈዋል ተብለው በተከሰሱበት ወቅት በማያሚ ፖሊስ ዲፓርትመን ውስጥ ያለውን ሙስና ለመመርመር ከህጉ ውጪ ለመሄድ ሲገደዱ እና ጉዳዩን ለማጣራት የሚያደርጉትን ጥረት በሳቅ እያዋዛ የሚያቀርብ ፊልም ነው ፡፡ ሰርቶ ለመጨረስም መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በመጪው የፈረንጆች ሰኔ ሰባት ለእይታ ይበቃል ተብሏል ፡፡
Inside Out 2

በአኒሜሽን ፊልም ጽሁፎቿ በምትታወቀው በሜግ ሌፋቭ እና ዴቭ ሆልስታይን ተጽፎ በ Walt Disney Pictures ፕሮዲዩስ የተደረገው Inside Out ሁለት የተሰኘው አኒሜሽን ፊልም በመጪው ሰኔ ወር ለእይታ ይበቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ፊልሞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
የመጀመሪያው የፊልሙ ክፍል የሚያጠነጥነው አንድ ቤት በመቀየሩዋ የተበሳጨች በአስራዎች የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው ታዳጊ ሀዘን ፣ ብስጭት ፣ ፍርሃት እና እንደ ቁጣ ያሉ ስሜቶች በአዕምሮዋ ውስጥ ሲጨቃጨቁ የሚያሳይ ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ አዳዲስ ስሜቶች በዋናነት ደግሞ የጭንቀት ስሜት ሲጨመር የሚያሳይ ፊልም ነው ፡፡ ፊልሙም በፈረንጆቹ ሰኔ 14 ለእይታ ይበቃል ተብሏል፡፡
Horizon: An American Saga – Chapter 1

ሌላኛው በሰኔ ወር ሊታዩ ከሚገባቸው ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ የምናገኘው Horizon: An American Saga – Chapter 1 የተሰኘውን ፊልም ነው ፡፡ ፊልሙም ወደ ኋላ ተመልሶ ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት በፊት እና ከጦርነቱ በኃላ ያለውን የምዕራብ አሜሪካዊያንን መስፋፋት እና ሰፈራ የሚያሳይ ነው።
በታዋቂው አሜሪካዊ ተዋናይ፣ ጸሀፊ እና ፐሮዲዩሰር ኬቪን ኮስትረ ተጽፎ በራሱ ዳይሬክት ተደርጓል ፡፡ ዋናውን ገጸባህሪም ኬቪን ኮስትረ፣አቢ ሊ፣ሲና ሚለር እና ሌሎች ተሳትፈውበታል፡፡ Horizon: An American Saga – Chapter 1 ከሁለት ቀናት በፊት ለእይታ በቅቷል፡፡ ኬቪን ኮስትረ የፊልሙ ሌሎች ሶስት ተከታታይ ክፍሎች በቀጣይ ወራት ለእይታ እንደሚበቁ ተናግሯል፡፡
The Watchers

አንዲት የ28 አመት ወጣት በአየርላድ በሚገኝ አስፈሪ ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ መኪናዋ ይበላሽባት እና ትወርዳለች፡፡ በጫካ ውስጥም በምታገኘው ቤት ስትገባ ከማታውቃቸው ሶስት ሰዎች ጋር በማይታወቁ ፍጥሮች ከታሰረች በኃላ ለማምለጥ የሚያደርጉትን ሙከራ የሚያሳይ አስፈሪ ፊልም ነው The Watchers፡፡ ፊልሙ ከAM Shine መጽሃፍ መነሻውን አድርጎ እንደተሰራ ተነግሯል ፡፡ ፊልሙ የአንድ ሰአት ከ 42 ደቂቃ እርዝማኔ ሲኖረው ከሰኔ ሰባት ጀምሮ ለእይታ ይበቃል ተብሏል ፡፡
A Quiet Place: Day One

በሚካኤል ሳርኖስኪ ተጽፎ ዳይሬክት የተደረገው A Quiet Place: Day One ሌላኛው በሰኔ ወር ለእይታ ይበቃል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ያለ ፊልም ነው ፡፡ አስፈሪ ዘውግ ያለው ፊልሙ ከዚ ቀደም ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት በርካታ አለም አቀፍ ተመልካቾችንም ማትረፍ ችሏል፡፡ አዲሱ ክፍልም ከቀደመው ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያለው ሲሆን አዲስ ገጸባህሪያትን አካቷል፡፡ ፊልሙ ከሌላ አለም ተወርውረው በኒዊውዮርክ ከተማ በሚወድቁ ኢሊየኖች ምክንያት ትርምስ ሲፈጠር ይጀምራል፡፡ ገጸ ባህሪያቱም ከእነዚህ ድምጽ ከማይፈልጉ ፍጥረቶች ለመደበቅ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያሳይ ነው ፡፡ፊልሙም የሰው ልጆች ሊስማሙ ከማይችሉት ነገር ጋር እንዴት እንደሚስማሙ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ ሴኔ 27 ለእይታ ይበቃል፡፡
በ-የአብስራ ብርሀኑ












