፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 23 2016| NBC ETHIOPIA-በመሬት ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት በዓለም ላይ ካሉ ትናንሽ አገሮች አንዷ ናት ቱቫሉ
ባላት የመሬት ስፋት በዓለም ላይ ሶስተኛ ትንሿ ሀገር ነች። በዩናይትድ ኪንግደም ስር የነበረችው ይህች ሀገር ነጻነቷን ያወጀችው እ.ኤ.አ በ1978 ነበር፡፡
ቱቫሉ በደቡብ ፓስፊክ ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ትናንሽ ደሴቶችን አቅፋ የያዘች ትንሽዬ ሀገር ናት።
እ.ኤ.አ በ1568 እስከ 1595 በስፔናዊው አሳሽ አልቫሮ ሜንዳና ዴ ነይራ እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ቱቫሉ በርካታ አስደናቂ ነገሮችን በውስጧ ይዛለች።
የሀገሪቷ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት አስራ አንድ ሺ አምስት መቶ የሚደርስ ሲሆን አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 26 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። በአለም ላይ ካሉ ትናንሽ አገሮች ተርታ ብትመደብም ሀገሪቷ ለቱሪስት መዳረሻ ሚሆኑ ድንቅ ስፍራዎችን አቅፋ ይዛለች፡፡
ቱቫሉ በአለም አቀፍ ደረጃ በማራኪ ገጽታዋ፣ በውብ የባህር ዳርቻዎቿ ፣ በልዩ የአትክልት ስፍራዎቿ፣ በዜጎቿ ለየት ባለ የአኗኗር ዘይቤ፣ ተወዳጅ በሆነው ዳንስ እና ሙዚቃ እንዲሁም በእደ ጥበባት ሞያ በይበልጡ ትታወቃለች፡፡
የአለም ሀገራት አሁን ላይ በቴክኖሎጂ እየተሸቀዳደሙ ካሽ ለስ ሶሳይቲ ወይም ከጥሬ ከንዘብ ንክኪ ነጻ የሆነ ምህዳር ለመፍጠር ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ቢሆንም በቱቫሉ ግን አውቶሜትድ ቴለር ማሽን ኤትኤም ፈጽሞ የለም፡፡

በቱቫሉ የሚገኙ ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎች እና ሆቴሎች ቪዛ ካርድ እና መሰል የኤትኤም ካርዶችን አይቀበሉም፡፡ በዚህም ወደ ሀገሪቱ ለመጓዝ ያሰበ ማንኛውም ቱሪስት የአውስትራሊያ ዶላር መያዝ ግድ ይላቸዋል፡፡
በቱቫሉ የጦር ሰራዊት የሚባል ነገር የለም። መደበኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሉም። አጠቃላይ ሀገሪቱ ወታደራዊ ተቋም የላትም።
ቱቫሉ በዓለም ላይ ካሉ አነስተኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች። ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጂዲፒዋ 42 ነጥብ 59 ሚሊዮን ዶላር ነው።
ደሴቶቹ ውስጥ ቋሚ ደሞዝ የሚከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች ብቻ ናቸው። የሀገሪቷ ህዝቦች ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው። የሃገሪቷ ኢኮኖሚ የተመሰረተው ከብት እርባታ እና አሳ ማጥመድ ዘርፍ ላይ ነው፡፡
ቱቫሉ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበት እና ልዩ ባህል ያላት ትንሼ ደሴታማ ሀገር ነች። ቱቫሉውያን በደሴት ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው በጀልባ መቅዘፍ ይበልጡኑ ይታወቃሉ፡፡
አትክልቶችን መንከባከብ ፣በእጅ ከተሠሩ ታንኳዎች ዓሣዎችን ማጥመድ፣ባህላዊ ሙዚቃ እና ውዝዋዜ እንዲሁም እግር ኳስ በሀገሪቷ ተወዳጅ ተግባራት ናቸው።

ቱቫሉ ባህላዊ የሆነ የማህበረሰብ ስርዓት አላት። በህብረት ቤት መገንባት እና እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ዓሣ ማጥመድ አይነት የመሳሰሉት ተግባራት የማከናወን ግዴታ አለበት። ባህላዊ ሥርዓቶችን ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ ናቸው ብለውም ያምናሉ፡፡
ቱቫሉ ከባህር ጠለል በላይ ከፍታዋ በአማካኝ አራት ነጥብ ስድስት ሜትር ብቻ ነው። ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚመጣ የትኛውም አደጋ በጣም ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
በዚህም ወደ ቱቫሉ የሚጓዙ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲያሽቆለቁል ሆኗል፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ከፍታዋ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊጠፉ ከሚችሉ ደሴቶች ዝርዝር ውስጥ እንደተካተተች የወጡ ሪፖርቶች በማመላከታቸው ነው ወደ ሀገሪቷ የሚያቀኑ ጎብኚዎች ቁጥር የቀነሰው፡፡
አገሪቷ ባላት መልካዓምድራ አቀማመጥ ሳቢያ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎችን ታስተናግዳለች፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ክስተቶች የደሴቲቱ ስነ-ምህዳር ሚዛኑን እንዳይጠብቅ እና ለነዋሪዎች ህይወትም አስጊ እና አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል።
በአሁኑ ጊዜ በቱቫሉ TTC የተሰኘ ብቸኛ የቴሎኮም አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ የመንግስት ተቋም ነው፡፡ TTC በእያንዳንዱ የቱቫሉ ደሴት በተከላቸው የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ደሴቲቷን ከጫፍ እስከጫፍ ማገናኘት ችሏል፡፡
በቱቫሉ 12 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን በእያንዳንዱ ደሴቶች ዘጠኝ የመንግስት እና ሶስት የግል ትምህርት ቤቶች አሉ።

በርካታ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ሀገራት ከሚያሟሉት መሰረተ ልማት በተጨማሪ ቅንጡ ሆቴሎችን ይገነባሉ፡፡ የቱሪስቶችን ፍሰት ለመጨመርም የሆቴሎቻቸው ቁጥር በርካታ ነው፡፡፡
ይህ በቱቫሉ ግን የተለየ ነው፡፡ በሃገሪቷ የሚገኘው አንድ ብቸኛ ሆቴል ነው፡፡በዋና ከተማዋ በፉናፉቲ አውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ የሚገኝ ሲሆን ቫያኩ ላንጊ ተብሎ ይጠራል፡፡
በ- ሀይማኖት ወርቁ












