፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 22 2016| NBC ETHIOPIA- በዕለት ተለት ህይወታችን ከማዕዳችን ፈጽሞ የማይለይ የማዕድ ድምቀት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ከሀብታም እስከ ዝቅተኛ ኑሮ ባላቸው ቤት የማይጠፋ ከውሀ በመቀጠል በዓለም ዙርያ ሰዎች አብዝተው የሚጠቀሙት ትኩስ መጠጥ ነው። ሻይ
ለሰዎች ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ በርካቶች የሆድ ሆዳቸውን ለመጨዋወት ‹‹ሻይ ቡና እንበል›› ሲሉም ይደመጣል፡፡
ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳለው የሚነገረው ሻይ ወደር የሌለው የዓለማችን ምርጡ መጠጥ ነው ሲሉ በርካቶችም ያሞካሹታል።
ታዲያ ይህ የብዙዎች ምርጫ የሆነው ሻይ ከየት ተገኘ ብለው ጠይቀው ከሆነ መልሱ ወደ ሩቅ ምስራቅ ያመራል።
አፈታሪክ እንደሚያስረዳው ሻይ ለመጀመሪያ ጊዜ መጠጣት የጀመረው ከ5 ሺህ አመት በፊት በቻይና ነበር። በ2737 የወቅቱ የቻይና ንጉሠ ነገሥት ሼን ኑንግ በሻይ ቅጠል ዛፍ ስር ውሃ ሲያፈሉ ቅጠሉ ወደ ማፍያው ገብቶ የውሃውን ቀለም እና መዓዛን ስለመለወጡ ይነገራል። ቀለሙ እና ጣዕሙ በቻይናው ንጉሰ ነገስት የተወደደው ቅጠል አሁን ላይ ሻይ ብለን እንጥራው እንጂ በወቅቱ የነበረው የዛፍ ስም ካሜሊያ ሲነንሲስ ይሰኝ ነበር።

ፖርቹጋል እና ደች በ1610 ለመጀመሪያ ጊዜ ሻይን ወደ አውሮፓ ያመጡ ሀገራት ናቸው ። በእንግሊዝ ውስጥ ሻይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው ደግሞ በንጉስ ቻርለስ ሁለተኛ ሰርግ ላይ መሆኑ ይነገራል፡፡
በንጉሠ ነገሥቱ ሼን ዮንግ የተወደደው ሻይ እያለ መላው ቻይናን ብሎም ፣ በጃፓን በአሜሪካ እንዲሁም በመላው ዓለም ተዳረሰ፡፡
እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ሁሉም ቻይናውያን ይጠቀሙት የነበረው የሻይ ዝርያ አረንጓዴ ሻይ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሻይ ተፈላጊነት እየሰፋ እና የውጭ ንግድ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሻይ ቅጠል ዝርያዎች እየተበራከቱ እና ጣዕምና ምርታቸው እየታከለበት ሄደ፡፡
ሻይ በዓለም ላይ ከውሃ ቀጥሎ ሰዎች በብዛት የሚጠቀሙት ሁለተኛው መጠጥ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከ1,500 በላይ የተለያዩ የሻይ ቅጠል ዝርያዎች ይገኛሉ ። የሻይ ተክሎች በእስያ ክፍሎች ባሉ በደኖች በስፋት ይበቅላሉ። ከ 25 በላይ አገሮች ደግሞ ሻይን እንደ ተክል በማምረት ኢኮኖሚያቸውን ይደግፉበታል፡፡
ዘርፈ በዙ ጥቅሞች እንዳሉት የሚነገርለት ሻይ ትኩረትን ለመሰብሰብ ፣ዘና ለማለት ፣ ስኳርን ለመቆጣጠር እንዲሁም በርካታ የጤና ጥቅሞች አሉት፡፡
የሻይ ተክል በአሁኑ ጊዜ በአራት ትልልቅ ሻይ አምራች አገሮች በሆኑት፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ስሪላንካ እና ኬንያ በብዛት ይመረታል። ሀገራቱ የዓለምን 75 በመቶ የሻይ ምርት ይሸፍናሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀን ሦስት ቢሊዮን ኩባያ ሻይ እንደሚጠጣ ይገመታል። አሁን ላይ በዓመት የሚመረተው የሻይ መጠን ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቶን የደረሰ ሲሆን፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር በዓመት ከ3 በመቶ በላይ እያደገ ስለመሆኑም ይነገራል።
በአለም ላይ ሻይ በመጠጣት ቀዳሚዎቹ ቱርካውያን ናቸው። ከ10 ቱርካውያን ዘጠኙ ሻይ እንደሚጠቀሙ ጥናቶች ያመልካታሉ።
እንደ አለም የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ በ2022 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ሻይ ተመርቷል፡፡

በሻይ ተክል ምርት ላይ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብም አሁን ላይ የትየለሌ ደርሷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2025 134 ቢሊየን ዶላር የሻይ ተክል ምርት ላይ ፈሰስ የሚደረግ ገንዘብ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡
በዓለም ላይ ካሉት በጣም ውድ የሻይ ዝርያዎች የቻይናው ዳ ሆንግ ፓኦ ቁጥር አንዱ ሲሆን፣ እንደየጥራት ደረጃው የዳ ሆንግ ፓኦ ሻይ ቅጠል በኪሎ ከሺዎች እስከ አስርሺዎች ዶላር ይሸጣል።
በ- ሀይማኖት ወርቁ












