፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 21 2016| NBC ETHIOPIA- ልቦለድ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶች እንዲሁም ምዕናባዊ ፈጣራዎች በጣፈጠ የአጻጻፍ ለዛ ተሰፍተው ለአንባቢያን የሚቀርብበት የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ የሆነ የኪነጥበብ ዘርፍ ነው።
በየዘመናቱ ለአንባቢያን የሚደርሱ በርካታ የልብ ወለድ ስራዎች ከዘመን ዘመን በመሸጋገር አይረሴ ሆኖው መዝለቅ ችለዋል። የግዜ መርዘም ካላደበዘዛቸው እና ትልቅ ማህበራዊ ተፅእኖን ማሳደር ከቻሉ እንዲሁም የበርካቶች ቀልብን መግዛት ከቻሉ ከዓለማች ምርጥ ልቦለዶች መካከል የተወሰኑትን መርጠን እናስቃኛችሁ።
1, አና ካሬኒና (Anna Karenina)

ዘመን የማይሽረው ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የዘለቀ ድንቅ ስራ ነው ሲሉ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በሩሲያው ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ የተጻፈ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ከ1875 እስከ 1877 በተለያየ ክፍሎች የታተመ እና ከዓለም የሥነ-ጽሑፍ ስራዎች መካከል ቁንጮ መሆን የቻለ ነው፡፡
አና ካሬኒ የተሰኘው ልብወለድ ዛሬም ድረስ በብዙ አንባቢያን ዘንድ ከአእምሮ ከማይጠፋ ድንቅ ልቦለዶች አንዱ ነው፡፡ ልቦለዱ በስምንት ምዕራፎች የተሰደረ ሲሆን፣ የሁለት ዋና ገጸ-ባህሪያትን ታሪክ ይተርካል። ታሪኩም አና የተባለች ኮረዳ አሌክሲ ኪሪሎቪች ከተባለ አንድ ባለጸጋ ወጣት ጋር ከጋብቻ በፊት በፈጠሩት ግንኙነት የደርስባቸውን ማህበራዊ ውጣውረድ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
አና ካሬኒና ልቦለድ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሩሲያ ውስጥ የነበረን ፍቅርን, ታማኝነትን እና የህብረተሰብን ግንኙነትን ይዳስሳል።
በልብ ወለዱ ከትዳር ውጪ የሚደረጉ የፍቅር ግንኙነቶች የሚያስከፍሉትን ዋጋ ፣ ከማህበረሰብ እሴት ያፈነገጡ ተግባራት የሚያስከፍሉት ዋጋ በጉልህ ተነስተውበታል፡፡
በሌላ በኩል መጽሀፉ በሩሲያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የባላባት ቤተሰቦች ወግ አጥባቂ ማህበራዊ አኗኗሮችን ይተቻል።
ልቦለዱ በዓለም ላይ ታዋቂነት እና ዝናን እንዲያገኝ፣ የልቦለዱ ግጭት፣ መቼት፣ እንዲሁም ጥልቀት የደራሲው የታሪክ ፍሰት አሰዳደር እና ሌሎች የልቦለድ አላባውያን ጥራት በዓለም የስነ-ጽሑፍ ታሪክ ትልቅ ስኬት እንዲገኝ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
የአና ካሬኒና ልዩ ገጸ-ባህሪያት እና ትረካ ሙሉ በሙሉ የደራሲው የምናባዊ ፈጠራዎች ናቸው። ቶልስቶይ ስለ ሩሲያ ማህበረሰብ ያለውን ጥልቅ ግንዛቤ፣ ስለራሱ ግላዊ ገጠመኞች እና ስለ ሰው ተፈጥሮ ያለውን ጥልቅ ምልከታ ተጠቅሞ ይህን አስደናቂ ልቦለድ ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡ ልቦለዱ ከዓመት ዓመት በተወዳጅነት የዘለቀ ድንቅ ሥራ መሆን ችሏል።
ልቦለዱ ከምን ጊዜም ከፍተኛ ሽያጭ ካላቸው መጽሃፎች አንዱ ሰለመሆኑም መረጃዎች ያመላክታሉ። ልቦለዱን መሰረት አደርገውም በርካታ ፊልሞች ተሰርተዋል።
2, ቱ ኪል ሞኪንግበርድ (To Kill a Mockingbird)

ሞኪንግበርድን ልቦለድ እ.ኤ.አ በ1960 በአሜሪካዊቷ ደራሲ ሃርፐር ሊ የተደረሰ ተወዳጅ የዓለማችን ልቦለድ ነው። ሞኪንግበርድን ልቦለድ እትሙ ለአንባቢያን ከደረሰ ከአንድ አመት በኋላ የፑሊትዘር ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል።
ልቦለዱም ጊዜ የማይሽረው የሥነ-ምግባር፣ የፍትህ እና የሰውን ሁኔታ ከሚዳስሱ የዓለማችን ታላላቅ ልብ ወለዶች ተረታ የተቀመጠ ነው።
በዓለም ዙሪያ ከ40 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎችን በመሸጥ ከምን ጊዜም ከፍተኛ ሽያጭ ካላቸው ልብ ወለዶች ተርታ መሰለፍ ችሏል፡፡
ልቦለዱ በጊዜው የነበሩትን ታዋቂ ማህበራዊ ጉዳዮችን ማለትም የዘር እኩልነትን እና የሞራል ትምህርትን ይዳስሳል።
ልቦለዱ በደቡብ አሜሪካ በወቅቱ ስለነበረው ታላቅ የኢኮኖሚ ውድቀት እና የቀለም ልዩነትን ተከትሎ የሚደረጉ መገለል እና አድሎዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ቢሆንም፣ የታሪኩ ገፀ-ባህሪያት፣ ሁነቶች እና ሴራዎች ሙሉ በሙሉ የምዕናብ ታሪኮች ናቸው።
ልቦለዱም እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ በነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት በሜይኮምብ ፣ አላባማ ከተማ ስላደገች ወጣት ልጅ ታሪክ ያስነብባል። የወጣቷ አባትም በከተማዋ ስር የሰደደ የዘር ጭፍን ጥላቻ ቢኖርም በወንጀል የተከሰውን ጥቁር ሰው ለመከላከል በጀግንነት ለፍትህ እና ለነጻነት የሚደረግ ትግልን ይተርካል፡፡
መጸሀፉም የዘር መድልዎ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በሚያስደንቅ ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ ነው።ልቦለዱን መሰረት የተሰራ ፊልም ተወዳጅነት ማትረፍ ችሏል፡፡
የደራሲዋ የተዋጣለት አተራረክ፣ የልቦለዱ የጭብጥ ጥልቀት፣ በታሪክ የተመሰረተ ግን ዘመን የማይሽራቸው ግንዛቤዎች እና የማይረሱ ገፀ ባህሪያቶቹ ጥምረት ልቦለዱ እስከ ዛሬ ድረስ ተጽኖ ፈጠሪ እና ተወዳጅ ሆኖ እንዲቀጥል አስተዋጾ አድርጓል።
3, ዘ ግሬት ጋትቢ ( The Great Gatsby)

The Great Gatsby እ.ኤ.አ.በ1925 በአሜሪካዊው ጸሃፊ ኤፍ.ስኮት ፊዝጀራልድ የተደረሰ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ ስራዎች መካከል አንዱ እና ዘመን አይሽሬ ድንቅ መጸሀፍ ነው።
ታሪኩ በ1920ዎቹ በኒውዮርክ ሲቲ መቼቱን አድርጓል።ሚስጥራዊው ሚሊየነር ጄይ ጋትስቢን እና የቆንጆዋን ዴዚ ቡቻናንን የፍቅር ታሪክ ይዳስሣል። ይህ ልብ ወለድ በበርካታ በአንባቢ ትውልዶች ዘንድ አድናቆትን አግኝቷል።
የፊዝጄራልድ ልዩ ጽሑፍ፣ የልቦለዱ የጭብጥ ጥልቀት፣ እና ዘላቂ የባህል ተፅዕኖው ጥምረት ልቦለዱን እውነተኛ የአሜሪካ የሥነ-ጽሑፍ ክላሲክ አድርጎታል።
እ.ኤ.አ በ1925 ለአንባቢያን የደረሰው ልቦለዱ የወቅቱን የነበሩትን ማህበራዊ ጉዳዮች ፣ የፍቅር ህይወትን ፣ ዓመፅን እንዲሁም የጨቋኝ ባለሀብቶች ድርጊት እና ያስከተለባቸውን አሉታዊ መዘዝ ያስነብባል።
The Great Gatsby ልቦለድ በዓለም ዙሪያ ከ 25 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች ተሽጠውለታል። ልቦለዱን መሰረት አደርገውም በርካታ ፊልሞች ተሰርተዋል።












