፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 21 2016| NBC ETHIOPIA-የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በወቅታዊ የክልሉ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በክልሉ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው የትኩረት መስክ የግብርና ልማት ሥራ መሆኑን አብራርተዋል። ከባለፉት ዓመታት አኳያ ቀደም ብሎ የግብርና ግብዓት ለማቅረብ መሠራቱንም ተናግረዋል። በብዛት፣ በወቅቱ በማድረስ እና በዋጋ ከባለፉት ዓመታት አንጻር የተሻለ መሆኑንም ገልጸዋል።
መሠረታዊ የሆነ የአቅርቦት ችግር አይኖርብንም፣ ችግሩ ስርጭት ላይ ነው፣ ዋናው ግብ ደግሞ ለአርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ ማድረስ ነው ብለዋል። የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በተገቢው መንገድ ለማሠራጨት ችግር መኖሩንም ተናግረዋል። ችግሮችን ለመፍታት መሥራት ይገባልም ብለዋል። በቂ ምርጥ ዘር መሰባሰቡንም ገልጸዋል።
ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለማነቃቃት ጥረት መደረጉንም አመላክተዋል።በክልሉ ሀገራዊ እና ክልላዊ የትምህርት ፈተናዎችን መስጠት የሚቻልባቸውን እና የማይቻልባቸውን አካባቢዎች ለይተን እየሠራን ነውም ብለዋል። ፈተናዎችን ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ግጭቱን ተከትለው የተከሰቱ የሙስና እና ሕገ ወጥ ተግባራት መኖራቸውን ነው የተናገሩት። መሬትን በጅምላ የማስተላለፍ እና ተደራጅቶ ለመዝረፍ የሚደረግ ሙከራ እንደነበርም አንስተዋል። ከመሬት ጋር የተያያዘውን ችግር ለማስተካከል የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ከመሬት ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ አካላትን በሕግ ጥላ ሥር አውለናል ነው ያሉት።
በሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሠማሩ አካላትን በተገቢው መንገድ ለመታገል እየሠራን ነው ብለዋል። የክልሉን ወቅታዊ ችግር ተጠቅሞ ለግል ጥቅሙ በሕገወጥ ተግባር ላይ የሚሠማራን አካል አምርረን መታገል አለብን ነው ያሉት። ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመኾኑ ሕግወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እድል እንደሚሰጥ ማመላከታቸውን ከአማራ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












