፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 08 2016| NBC ETHIOPIA- ለረጅም አመታት ከዘለቁ የእርስ በእርስ ጦርነቶች መካከል የሚጠቀስ ነው በአፍጋኒስታን የተካሄደው ጦርነት፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1978 ጀምሮ እስከ 1992 ለአስራ አራት አመታት የተካሄደው ይህ የእርስ በእርስ ጦርነት ቀላል ለማይባሉ ውድመቶች መንስኤ ሆኗል፡፡
በደቀቀ ኢኮኖሚ እና በማይጠቀስ የፖለቲካ ስርዓት የቆየችው ሀገረ አፍጋኒስታን ወደ እርስ በእስር ጦርነት የከተታት ፖለቲካዊ ጽንፍ ነው፡፡
በአፍጋኒስታን የነበረው ጦርነት በሀገሪቱ ታሪክ በ1978 በፀረ-ኮምኒስት ተዋጊዎችና በአፍጋኒስታን ኮሚኒስት መንግስት መካከል የተካሄደ ነው፡፡
ለጦርነቱ መነሻ የሆነው በኑር መሀመድ ታራኪ የሚመራው ግራ ዘመም ወታደራዊ መኮንኖች በፕሬዚዳንት መሀመድ ዳውድ የሚመራው መንግስት በ1978 ከስልጣን መውረድን ተከትሎ ነው።

በ1978 የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎም የሩሲያ ሀይሎች ወደ አፍጋኒስታን የገቡ ሲሆን ከስምንት አመታት የአፍጋኒስታን ቆይታ በኋላ ሀገሪቱን ለቀው መውጣት የጀመሩት ግንቦት 15 1988 በትላንት ዕለት ነበር፡፡
በታህሳስ 1979 የሶቪዬት ህብረት ወታደሮች ወደ አፍጋኒስታን በመግባት በውስጣዊ አመጽ የመጣውን ኮሚኒስቱን የሶቪየት ህብረት ደጋፊ መንግስትን ለማጠናከር እንደነበር ይነገራል።
በአጭር ጊዜ ውስጥም 30 ሺህ የሚጠጉ የሩስያ ወታደሮችና ድጋፍ ሰጪ ቁሳቁሶች ወደ አፍጋኒስታን ይጎርፉ ጀመር፡፡
ይህንንም ተከትሎ የአፍጋኒስታን ተፋላሚዎች የራሳቸውን ሀገር የኮሚኒስት መንግስትና የሶቪየት ወታደሮችን ይደግፋሉ ከሚሉ አማፂያን ጋር እልህ አስጨራሽ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡
የሶቪየት ወታደሮች ተፋላሚዎችን በተለያዩ ዘዴዎች ለማጥፋት ቢሞክሩም ውጊያው በሽምቅ የሚካሄድ በመሆኑ ተዋጊዎቹ ከተቃጣባቸው ጥቃት ለመትረፍ ችለዋል፡፡
ከዚያም ሶቪየቶች የገጠር አካባቢዎችን በቦምብ በማፈንዳት የሙጃሂዲኖችን የሲቪል ድጋፍ ለማጥፋት መሞከራቸውን ተከትሎ በርካታ ንጹሃን ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
በ1982 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ዜጎች በፓኪስታን ጥገኝነት ሲጠይቁ ሌሎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ወደ ኢራን ተሰደዋል።
በቀጣዮቹ ስምንት አመታት ውስጥ ሁለቱ ወገኖች ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ሲፋለሙ ቢዘልቁም ሶቪዬቶችም ሆኑ ሌሎቹ ተዋጊዎች ወሳኝ የሚባልን ድል ማግኘት አልተቻላቸውም፡፡

የዛኔዋ ሶቪየት ህብረት ወይም ሩሲያ በአፍጋኒስታን በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት ጣልቃ መግባት ዋጋ እንዳስከፈላት ይታመናል፡፡
ሶቪየቶች በአፍጋኒስታን ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የሟቾችን ቁጥር ይፋ ባያደርጉም የዩኤስ የስለላ ምንጮች እስከ 15 ሺህ የሚደርሱ የሩስያ ወታደሮች ወዳ በገባችበት ጦርነት ሳቢያ እንደተገደሉባት ተዘግቧል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቀድሞውንም በሁለት እግሩ ለመቆም በተቸገረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራን ተከናንቧል፡፡
ሶቬት ህብረት ወደ አፍጋኒስታን መግባት የተሳሳተ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ከሚለው ወቀሳ በዘለል ከአሜሪካ ጋር ያላትንም ግንኙነት በእጅጉ ጎድቶታል፡፡
በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ጂሚ ካርተር የሩስያን ድርጊት ክፉኛ ተችተዋል፡፡
እናም የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ከማውጣትም አልፈው በ1980 በሞስኮ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለትን ኦሎምፒክ እንዲታገድ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ሶቬየት ከተለያዩ የአለም ሀገራት እየደረሰባት ያለውን ጫና ተከትሎ በ1988 ወደ ጦርነት በገባችበት እግር ለመውጣት ወሰነች፡፡
በ1988 አሜሪካ፣ ፓኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ሶቪየት ህብረት ወደ አፍጋኒስታን የገቡ ወታደሮችን ለማስወጣት ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ስምምነቱንም ተከትሎ ግንቦት 15 1988 ልክ በትላንትናው እለት ሞስኮ ወታደሮቿን ማስወጣት ጀመረች፡፡
ምንም እንኳን ሩሲያ ሀገሪቱን ለቃ ብትወጣም ጦርነቱ ግን እስከ 1992 ዘልቆ የተካሄደ ሲሆን በስተመጨረሻም ጸረ ኮሚኒስቱ ቡድን አፍጋኒስታንን ተቆጣጠረ፡፡
አፍጋኒስታን ሙሉ የሕዝብ ቆጠራ አካሂዳ የማታውቅ በመሆኗ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በሀገሪቱ የደረሰውን የሟቾች ቁጥር ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል፡፡
ነገር ግን ከሚቀመጡ ግምቶች መካከል የተሻለ የሚባለው ከ1992 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍጋኒስታናውያን ተገድለዋል፡፡
ምንም እንኳን በግጭቱ ወቅት የተገደሉት እና በተዘዋዋሪ በግጭቱ ምክንያት የተገደሉት ቁጥር ግልፅ ባይሆንም።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በአገሪቱ በተቀበሩ ፈንጂዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ሲል ታሪክ የእርስ በርሱን ግጭት ሰዋዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በማህደሩ ከትቦታል፡፡












