፨ ፨ ፨ ፨ ፨
ለ42 ቀናት የሚቆውና የአለማችን ግዙፉና ውዱ ምርጫ በማድረግ ላይ የሚገኙት ህንዳውያን በከፍተኛ ሙቀት እየተጠቁ ነው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ በህንድ በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት በመካሄድ በሚገኘው ምርጫ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑንም ዘገባው አያይዟል፡፡
ከፍተኛ የሙቀት መጠኑ በመራጮች ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንዲሁም የመራጮችን ስሜትን ሊያናውጥ ይችላል የሚሉ ጥናቶችም እየወጡ ነው፡፡ አንዳንድ የምርጫ እጩ ተወዳዳሪዎችም በሙቀቱ ሳቢያ ራሳቸውን እስከመሳት መድረሳቸውን አልጄዝራ ዘግቧል፡፡
በማዕከላዊ ህንድ የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስትር የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እንዳሉ ድንገት ራሳቸውን ስተው መወውደቃቸው የተገለፀ ሲሆን ከፍተኛ ሙቀት መጠኑም ምክንያት መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ የሚትሪዎሎጂ ኤጀንሲ ቀደም ሲል በግንቦት የሙቀት መጠኑ ከመደበኛው በላይ ሊሆን ይችላል ሲል አስጠንቅቆ የነበር ሲሆን በደቡብ ራጃስታን፣ ምዕራብ ማድያ ፕራዴሽ እና ጉጃራት የሙቀት መጠኑ ከመደበኛ በላይ ሆኖ ተመዝግባል፡፡
በዚህም በምስራቃዊ ህንድ አማካይ የሙቀት መጠን በሚያዝያ ወር 28.12 ዲግሪ ሴልሺየስ የነበረ ሲሆን በተያዘው ወር ግን የሙቀት መጠኑ 45 ዲግሪ ሴልሺየስ መድረሱን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
የሀገሪቱ 970 ሚሊዮን መራጮች ፣ 15 ሚሊዮን የምርጫ አስፈፃሚዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ እጩዎች ከከባዱ የበጋ ወቅት ጋር እየታገሉ ምርጫውን እያካሄዱ ነው። ነገር ግን መራጮች በጎዳናዎች በሚደረጉ የፖለቲካ ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብራቸውን ሊያስተካክሉ ግድ ብሏቸዋል፡፡ በዚህም የምርጫ ቅስቀው ወደ ማለዳ እና ምሽት ቀይረውታል የተባለው ሲሆን የምርጫ ቅስቀሳ በሚደርጉበት ወቅትም ዣንጥላ፣ ኮፍያ እና የመጠጥ ውሃ እንዲይዙ ግድ ሆኖባቸዋል ፡፡ ሙቀቱ የማይቻል ነው፤ በጠራራ ፀሀይ ቅስቀሳ ማድረግ እጅግ ከባድ ሆኗል ሲሉም እጩ ተወዳዳሪዎችና መራጮች ተናግረዋል፡፡
የሕንድ አጠቃላይ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ በሚያዝያ እና በግንቦት የሚካሄድ ሲሆን መራጮች እና የምርጫ አስፈፃሚዎች ኃይለኛውን የበጋ ሙቀት ለመቋቋም ይገደዳሉ፡፡ ነገር ግን በዘንድሮ የተከሰተው የሙቀት መጠን ከቅርብ ዓመታት ብሎም ከሌሎች የእስያ ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግባል፡፡ ባሳለፍነው ሚያዝያ በሀገሪቱ በተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ቢያንስ 9 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

የምርጫ አስፈፃሚዎች ሙቀቱን ለመቋቋምና በሰዎች ላይ ጉዳት እንደይከሰት በምርጫ ጣቢዎቸ ውስጥ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ እና የምርጫ ጊዜያትን በማራዘም እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ተብሏል።
የዘንድው ምርጫ ከ2019 ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ሚያዝያ 19 እና 26 የተካሄዱት የመጀመሪያዎቹ ሁለት የምርጫ ደረጃዎች እያንዳንዳቸው ቢያንስ 3 በመቶ መራጮች ብቻ ተሳታፊ መሆናቸውን ተገልፃል፡፡ የተመዘገበው ከፍተኛ ሙቀት ለመራጮች ተሳትፎ መቀነስ ምክንያት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ጠቅሰዋል።
ከግንቦት 16 ጀምሮ በፑንጃብ፣ ኡታር ፕራዴሽ እና ሃሪያናን ጨምሮ በሰሜን ምዕራብ ክልል አዲስ የሙቀት ማዕበል ሊከሰት እንደሚችል የህንድ ሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡
የሙቀቱ ተጽዕኖ በምርጫው ሂደት ላይ ብቻ ሳይሆን የውሃ እጥረት፣ የሰብል መጎዳት እና የሃይል ፍላጎት ከፍ በማድረግ የሃይል እጥረት እንዲከሰትም ምክንያት ሆናል በሚል ቅድመ ትንቤ ተቀምጧል፡፡ በሀገሪቱ ከመደበኛ በላይ የሆነው የሙቀት መጠን በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተለ ነው፡፡
በሙቀት ውስጥ ረጅም ሰዓታትን ማሳለፍ የኤሌክትሮላይት ሚዛን መዛባትን ያስከትላል ይህ ደግሞ ድካም እና ማዞር እንዲሁም ራስን መሳት ያስከትላል ሲሉ ባለሙያዎች ገልፀዋል።
እንደ የልብ ሕመም ወይም የደም ግፊት ያሉ ተጓዳኝ በሽታዎች ያለባቸው ግለሰቦች ከሙቀት ጋር የተያያዙ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው ሲሉ የህክምና ባለሙያዎች ተናረዋል፡፡ በዚህም መራጮች የሙቀቱ ስጋት ቢያድርባቸውም ቅድመ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት 2023 ህንድ ከ1901 ጀምሮ ሁለተኛው ሞቃታማ ዓመት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በዛው አመት ወደ 264 የሚጠጉ ሰዎች በሙቀት ሳቢያ መሞታቸው የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡












