፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 10 2016| NBC ETHIOPIA-በአለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ መቀዛቀዞች እና የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ብሎም ጦርነቶች ተከትሎ የአለማችን ኢኮኖሚ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡
በአለማችን ሁለተኛዋ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ቻይናም ባለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት ያስመዘገበችው ኢኮኖሚያዊ እድገት ከአርባ ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መጠን መቀነሱ የቻይና ብሄራዊ የስታስቲክስ ቢሮ በ2023 ማብቂያ ላይ ባወጣው ሪፖርት ማመላከቱ ይታወሳል፡፡
አለም ባንክ ሀገሪቱ በ2024 ኢኮኖሚዋ ከባድ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችልና በ2023 ካስመዘገበችው 5 ነጥብ 2 በመቶ እድገት በተያዘው አመት ወደ 4 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ይላል ሲል ትንበያውን ከወራት በፊት ይፋ አስቀምጣል፡፡
ቻይናም በበኩላ ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ ከገባችበት የኢኮኖሚ መዋዠቅ ለመውጣትና እድገቷን ለማፋጠን የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ቀደም ብላ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በየካቲት 2024 የቻይና ብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ የሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) እድገት በ2023 ከነበረው ጭማሪ ሊኖረው እንደሚችል ቅድመ ግምቱን አስቀምጦ ነበር፡፤
ኤጀንሲው ይፋ ባደረገው መረጃም የቻይና ኢኮኖሚ በ2024 የመጀመሪያ ሩብ አመት ከተጠበቀው በላይ እድገት መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በ5 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን የሀገሪቱ ብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ አረጋግጧል፡፡

በሀገሪቱ የተመዘገበው ያልተጠበቀ ኢኮኖሚያዊ እድገት ካለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ከተመዘገበው የ5 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ጋር ሲነፃፀር በ1.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የተገለፀው፡፡
የቻይና ብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጠንካራ አመራር የኢኮኖሚው እድገት ጥሩ ጅማሮ አሳይቷል ብሏል።
የዓለም ፋብሪካ የሚል ስያሜ የተሰጠው የቻይና የኢንዱስትሪ ምርት 6.1 እና የግብር ዘርፉ 3.8 በመቶ ያደገ ሲሆን አገልግሎቶች ደግሞ በ5 በመቶ ማደጉን በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ከፈረንጆቹ ጥር እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ የፍጆታ ዕቃዎች የችርቻሮ ሽያጭ በ4.7 በመቶ ጨምሯል ፣ የገጠር ቤተሰቦችን ሳይጨምር ቋሚ ንብረቶች ላይ ኢንቨስትመንት 4.5 በመቶ አድጓል ብሏል ኤጀንሲው በመግለጫው፡፡ በአፃሩ በሪል ስቴት ልማት ላይ ያለው ኢንቨስትመንት ግን 9.5 በመቶ መቀነሱ ተጠቁማል፡፡
ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የወጡ ፖሊሲዎች ተፈጻሚነታቸውን መቀጠላቸው ብሎም በሀገሪቱ የምርትና ፍላጎት መጣጠም መጨመር ተከትሎ ለተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ምክንያት መሆኑም የኤጀንሲ መረጃ ይጠቁማል፡፡ እንዲሁም የቻይና ኢኮኖሚ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ውስጥ የተመዘገበው አዎንታዊ እድገት የተቀመጡ አመታዊ የልማት ግቦች ለማሳካት ጠንካራ መሰረት ጥላል ሲል ኤጀንሲው በመግለጫው አመላክቷል፡፡ ተቋሙ አክሎ እድገት እያሳየ ያለውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስቀጠል የተረጋጋና ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት እስካሁን ጠንካራ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል ሲል ቢሮው ገልጿል።
እንዲሁም በ2024 የመጀመሪያ ሩብ አመት ሀገሪቱ ያልተጠበቀ እድገትን ብታስመዘግብም በችርቻሮ እና በኢንዱስትሪ የተቀመጡ አመታዊ የዕድገት ግባቸውን ለማሳካት ከባድ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችልም ተጠቁመዋል።
ባለፈው ሳምንት፣ የኤዥያ ልማት ባንክ የቻይና ኢኮኖሚ በዚህ አመት 4.8 በመቶ እና በ2025 4.5 በመቶው እድገት ታስመዘግባለች ሲል ቅድመ ትንበያውን አስቀምጦም ነበር፡፡
የስራ አጥነት መጠን በየካቲት ወር ከነበረበት 5.3 በመጋቢት ወደ 5.2 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ይህ አሃዝ ግን በከተማ ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን ብቻ የሚያጠቃልል መሆኑ ተገልፃል፡፡
ቤጂንግ ባለፈው ወር ለ2024 የ5 በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ግብን አስቀምጣ በመንቀሳቀስ ላይ ስትሆን እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ 1.8 ትሪሊዮን ዶላር ለዋና ዋና የግንባታ እና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ወጪን ጨምሮ በርካታ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎችን ይፋ አድርጋለች

ቤጂንግ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ትልቁን የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ስታስተናግድ መቆየቷን በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ አሃዞች አመላካች ናቸው፡ በምትከተላቸው የቁጥጥር እርምጃዎች እና በከባድ የብሄራዊ ደህንነት ህግ የተነሳ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ባለፉት ግዜያት ማሽልቆልንም አሳይቷል፡፡ በቅርቡ ሀገሪቷ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከሀያሏ አሜሪካ መሪዎች ጋር ያደረገችው ምክክር የውጭ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሻሻል እንዲሁም ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት እየወሰደች ካለው እርምጃ አንዱ ማሳያ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቻይና የዘንድሮው የኢኮኖሚ ዕድገቷን 5በመቶ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች የምትገኝ ሲሆን እቅዱ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጻር ተመሳሳይ ነው ተብሏል፡፡ ቻይና የዓለምን ኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ምህዳርን በበላይነት ከተቆጣጠሩ ተቋማት እና ሀገራት ጋር ያደረገችው ምክክር ሀገሪቱ እያስተናገደች የምትገኘውን የኢኮኖሚ መዋዠቅ በማስቀረት ዳግም ምጣኔ ሃብቷን ከማሽቆልቆል ይታደገው ይሆናል የብዙ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መላምት ነው፡፡












