ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ-አባ መቻል
አዲስ አበባ | የካቲት 22፣ 2016| NBC ETHIOPIA – የጥቁር ህዝቦች ደማቅ ታሪክ፣ የሀበሻ ኩራት፣ የአድዋ ድል፡፡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ክብር በአድዋ የጦርነት ምድር ላይ የጀግንነት ታሪካቸውን በደማቅ አሻራ ከጻፉ ከአስራ ሁለቱ ዋነኛ የጦር አዛዦች መካከል ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡‹‹ከንጉሶች በታች ከራሶች በላይ›› በመባል ይታወቃሉ በፍርድ አሰጣጥ ጥበባቸዉ ሁሉም ይደነቅባቸዋል፡፡ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በማለት ሁሉን አቻችለው በማስማማትም ይታወቃሉ፡፡ በኢትዮጰያ ታሪክ የመጀመሪያዉ የጦር ሚኒስትር በመሆን ሹመትንም የተጎናጸፉ ስመ ጥር ባለታሪክ ናቸው፡፡ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ አባ መላ!!
ሀብተጊዮርጊስ በምዕራብ ሸዋ በጨቦ እና ጉራጌ አውራጃ 1844 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ከልጅነታቸዉ ጀምሮ በሳል እና ቀልጣፋ ነበሩ፡፡ ከ18 አመታችዉ ጀምሮ ዳግማዊ ዐፄ ሚኒሊክ ቤተ-መንግስት ገብተዉ በርካታ ሀላፊነቶችን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ሚያዚያ 30 ቀን 1874 ዓ.ም በተካሄደዉ እምባቦ ጦርነት ሀብተጊዮርጊስ ከፍተኛ ድርሻን በመያዝ ጀግንነታቸዉን አሳይተዋል፡፡ ለችግር መዉጫ መላ የማያጡት ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ በንጉሱ አባ መላ የሚል ቅፅል ስም ወጥቶላቸዋል፡፡ በፈረሳቸዉ በአባ መቻል መጠሪያ ስምም ይጠሯቸዋል፡፡
የመጀመሪያዉ ጦርነት ተንቤን ላይ ተካሄዶ ሳለ ሜጀር ሳልሳ የተባለ ጣልያን ዲፕሎማት ጦርነት መደረጉ ቀርቶ ከምጽዋ እስከ አላጌ ድረስ ያለዉ ሀገር ይሰጠን ብሎ የጣልያን ሀሳብ ለዐፄ ሚኒሊክ ባቀረበ ግዜ ነገሩን የሰሙ አብዛኛዉ የጦር አለቆቻቸዉ በጣልያን ሀሳብ ሲስማሙ ንጉሱ በመለኝነታቸዉ የሚተማመኑባቸዉ ፊታውራሪ ጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ወደሳቸዉ ላኩ፡፡ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስም እቴጌጣይቱ ጋር በመምከር የጠላትን የአመጣጥ ሁኔታና ሀሳብ አዉቀዉት ነበርና ‹‹የመጣነዉ ለጦርነት ነዉ ጠላት ሀገራችንን መያዙ ሲያሳዝነን እንደገና ልጨምር ሲል መፍቀድ ሀገሪቱን በሙሉ ጠቅልሎ ለመውሰድ እንጂ በዚህ ክልል ጣልያን መንግስት በቃኝ ይላል ማለት ዘበት ነዉ፡፡ይልቁንም ወታደራችን በቻለዉ አቅም ይግጠመዉ እና እግዚዓብሄር የሚሰጠንን እድል ብናይ ይሻላል›› በማለት ልቡ ወደ ጣልያን መንግስት ሃሳብ ያደላዉን የጦር አለቆች ሀሳብ በማስቀየር ወደአንድ አላማ መርተዋል፡፡
120 ሺህ አርሶ አደር በአንድነት የተሰለፈበት የአድዋ ጦርነት ሲታወጅ ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ አንድ መቶ ሀምሳ አጋሰስ የተጫነ ማር እንዲሁም በግዜዉ ከሚያስተዳድሩት የጨቦ ግዛት በ600 አጋሰስ የተጫነ ስንቅ ይዘዉ ከተወሰኑ ጦራቸዉ ጋር ሊዘምቱ ድንኳናቸዉን ተከሉ፡፡ ታዲያ ንጉሱ የስንቁን መሰናዶ፣ የወታደራቸዉን ዝግጅት፣ የፈጠሩትን መነቃቃት ባዩ ግዜ ‹‹ሀብተጊዮርጊስ ማለት ሰዉ ነዉ›› ብለዉ ከልባቸዉ አድንቀዋቸዋል፡፡
የመጀመሪያዉ የጦር ሚኒስትር ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ የኢጣሊያ ወራሪዉ ጦር ሀገርን ለመዉረር በቃጣዉ በዚያ ወቅት ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክን እና እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የጦሩ ፊታዉራሪ እና አዝማች ከነበሩት ፊታውራሪ ገበየዉ፤ አባ ጎራዉ ጋር እንዲሁም ዋና ዋና የጦር መሪዎች ጋር ግንባር ላይ በመሆን 3 ሺህ የሚሆን ጦራቸዉን ይዘዉ ደማቅ ታሪክ ፅፈዋል፡፡
ፊታዉራሪ ገበየዉ በአድዋ ጦርነት ላይ በተሰዉ ግዜ ከድል መልስ ንጉሱ በእሳቸዉ ምትክ የትኛዉን ጀግና ይሾሙ ይሆን ተብሎ በርካታ ለቦታዉ የሚመጥኑ የጦር አለቆች ሲጠበቁ ዐጼ ሚኒሊክ ከእነማዕረጉ የፊታዉራሪ ገበየዉን ቦታ ለፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሰጥተዉ የጦር አለቅነትን ሾሟቸው፡፡
አባ መላ ዘመናቸዉን እንደፊታዉራሪ፣ እንደ ጦር ሚኒስቴር እንዲሁም በወቅቱ ስያሜዉ ባይኖርም እንደጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነዉ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከንጉሱ ጋር በመጣመር በርካታ ግዛቶችን ወደ አንድነት ለማምጣት የፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ጦር ከራስ ጎበና ዳጬ፣ ከወሎ ራስ ሚካኤል አሊ እና ከባልቻ አባ ነፍሶ ጦር ጋር በአንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በአስገራሚ የዲፕሎማሲ እና የፍርድ አሰጣጣችዉ የሚታወቁት ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ የጨቦን አከባቢ ጨምሮ ሞያሌን፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ከደቡብ ምዕራብ እስከ ኬንያ ያስተዳድሩ ነበር፡፡ ከተሰጧቸዉ አከባቢዎች አንዱ የሆነዉ ቦረና ላይ እንግሊዞች ያለፈቃድ ወደግዛታቸዉ በኬንያ በኩል ገብተዉ ስለተገኙ ተገድለዉ ኖሮ አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆነዉ የእንግሊዝ መንግስት ቆንፂል ያለአግባብ ዜጎቼ ተገድለዉብኛል ሲል አቤቱታዉን ለዐፄ ሚኒሊክ አመለከተ፡፡ ንጉሱም መክረን እንነግርሃለን ካሉት በኋላ የእንግሊዙን ቆንፂል ወደአባ መላ እንዲሄድ አደረጉ፡፡
የእንግሊዙ ቆንፂል ወደፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ቤት ሄዶ ሰዎቻችን ያለአግባብ ተገድለዉብናል ደማቸዉ የፈሰሰበት መሬት ይሰጠን ባሉ ግዜ ፊታዉራሪ በሃገራችሁ ይህን መሳይ ደንብ አለ እንዴ ሲሉ ጠየቁ፡፡ አዎን ሲሏቸዉ ደግ እንግዲያዉስ እኛም የዐፄ ታዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ከዚህ ሄዶ በሀገራችሁ ተገድሎብናልና ለእኛም ሎንዶንን ስጡን ለእናንተም ይህን ዉሰዱ ብለዉ ቃል አርቅቀዉ ፈረሙና በል ፈርም ብለዉ አማራጭ አሳጥተዉ ልከዉታል፡፡
የፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ተደማጭነት እና ክብር በአፄ ሚኒሊክ ግዜ ብቻ ያበቃም አልነበረም፡፡ አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ ሹመት ሽረት ሲያደርጉ ስልጣንን ካለአግባብበ መጠቀም እና መሰል ችግር ፈጥረዋል የተባሉትን የዐፄ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስትሮች ከስልጣን ሲያስነሱ ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስን ደፍሮ የሚነካ አልነበረም፡፡
አባ መላ ዘመናቸዉን በጀግንነት ኖረዉ በደረሰባቸዉ ህመም ሳቢያ ታህሳስ 3 ቀን 1919 ከእዚህ አለም በሞት ተለዮ፡፡ በ76 አመታቸዉ ከዚህ አለም የተለዩት አባ መላ የሞቱባት እለት ታህሳስ ሶስት እለተ አርብ፤ ከንጉሱ ህልፈተ ህይወት ታህሳስ ሶስት እለተ አርብ 1906 ዓ.ም ጋር መግጠሙን ለአጼ ሚኒሊክ ካላቸዉ ታማኝነት እና ፍቅር ጋር አያይዘዉ ብዙዎች ይገረሙበታል፡፡
የንጉሶች በታች፣ የራሶች በላይ አባ መላ ቀብራቸዉ መድፍ ተተኩሶ፣ ነጋሪት ተጎስሞ በመናገሻ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ባለቤታቸዉ አልታየ ወርቅ፣ግርማዊት ንግስት ዘዉዲቱና አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ጨምሮ በርካቶች በተገኙበት ተፈፅሟል፡፡
በቀብራቸዉ ላይ ቅኔ አዋቂዉ አቶ ተሰማ ‹‹ከሚኒሊክ ይዞ እስከ አሁን ድረስ፣የአልታየ ሞት ሆነ የሀብተጊዮርጊስ›› ሲሉም ገጥመዉላቸዋል፡፡ ፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ በአዲስ አበባ መርካቶ በስማቸዉ ድልድይ እንዲሁም በቱሉ ቦሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ በስማቸዉ ተሰይሞላቸዋል፡፡
በ-ሜቲ ፋንታሁን












