አዲስ አበባ | የካቲት 15፣ 2016| NBC ETHIOPIA -የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ኩራት፤ ለአፍሪካውያውያን የነጻነት ምልክት ነው፡፡ ይህን ድልና ነጻነት ለማምጣት ከንጉሱ ጋር በመሆን ታላላቅ ጀግኖች ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ሀገርን የማዳን፤ ታሪክን የመሳል፤ ትውልድን የማሻገር፤ ጽናትንና የሀገር ፍቅርን በደማቁ ለማሳየት ታላላቅ ጀግኖች ከመላከ ሞት ጋር ተፋጠዋል፡፡ ከእነኚህ
መካከል ደግሞ አንዱ ራስ አባተ ቧ ያለው ንጉሱ ናቸው፡፡
ራስ አባተ ቧ ያለው አነጣጣሪው መድፈኛ፤የማያስቅምጥ የማያስተኛ፤ መላከ ሞትም ቢመጣ አገራቸውን ለመከላከል ከማይመለሱ የዳግማዊ ምኒልክ ዘመን አርበኞች መካከል በአድዋ ጠፈር ላይ በጣም ጎልተው ከሚታዩት አብሪ ኮከቦች መካከል ደማቁ የመንዝ ግዢው ጀግና ራስ አባተ ቧ ያለው (አባ ይትረፍ)አንዱ ናቸው።
በ1885ዓ.ም የተወለዱት ራስ አባተ በፈረስ ስማቸው አባ ይትረፍ የጦር ገበሬ፤ በሙያቸው የተመሰገኑ፤ የጦርን ትምህርት ተምረው መድፍን እንደ በትር በእጃቸው መዳፍ እንዳሻቸው የሚያደርጉ ነበሩ።
ራስ አባተ በአምባላጌ ጦርነት በመድፍ ውጊያ የወራሪውን ጦር ድባቅ መትተዋል፡፡ ከአስደናቂው የአምባላጌ ጦርነት ድል ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በተዋደቁበት የመቀሌው የእንዳ ኢየሱስ ጦርነት ራስ አባተ ውጊያን ከእነ መድፋቸው ገብተውበት ነበር ይባላል።
የእንዳ ኢየሱስን ምንጭ ማይ አንሽቲን በመክበብ የወራሪዎችን መድፎች አመድ በማድረግ ድል ላገኘንበት ጦርነት ታላቅ ባለውለታ ከሚባሉት የጦር መሪዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ራስ አባተ ነበሩ።

ራስ አባተ ከመቀሌው ድል በኋላ አምባላጌ ላይ በተማረከው መድፍ በመጨረሻው የአድዋ ጦርነት ጊዜ ተኩሰው በጠላት መድፍ አፍ ውስጥ አስገብተው የጠላት መድፍ ተኩሱን እንዲያቋርጥ ያደረጉ ጀግና ናቸው። ለዚህ ጀግንነታቸውም የሚከተለው ተገጥሞላቸዋል፡-
“ወንጌል ተምሯል ወይ ያባተ ፈረስ
ይትረፍ ለነገ አይል ምንም ቢደገስ፣
አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ ሰው
ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው፣
አበሻ ጉድ አለ ጣሊያን ወተወተ
አይነ ጥሩው ተኳሽ ቧ ያለው አባተ!”
አፄ ምኒልክ ጦራቸው መቀሌ ደርሶ ሰፈሩን ተከፋፍሎ ከያዘ በኋላ በጣልያን ምሽግ ዙሪያ ራቅ እያለ ሰፈረ። ድንኳን በሚተከልበትና ጭነት በሚራገፍበት ጊዜ አንድ በቅሎ ፈርጥጦ ወደ ጣልያኖች ምሽግ ሮጠ። አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ጣልያኖቹ የመድፍ ተኩስ ጀመሩ።
ጣልያኖቹ አብዝተው መተኮሳቸውን ንጉሰ ነገስቱ በተመለከቱ ጊዜ ሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለውን እና በጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎን ሂዱ እናንተም ተኩሱባቸው ብለው አዘዙ እና የምሽቱ ጊዜ በመድፍ ተኩስ አለፈ።
ወደ ማታ ንጉሱ እንደገና ሊቀ መኳስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻን ጠርተው “እነዚህን ጣልያኖች ከጉድጓዳቸው ሳላስወጣ የትም አልሄድም፡፡ እናንተም የጠላት መድፍ ጥይት የማይደርስበትን ስፍራ መርጣችሁ ከዚያ ሆናችሁ ምሽጉን በመድፍ ምቱት!” ብለው አዘዟቸው።
ሊቀ መኳስ አባተ ጦራቸውን ይዘው በምሽጉ በስተግራ የጣልያኖችን ቃፊር ጠባቂ አባርረው ምሽግ አበጅተው መድፍና መትረየሳቸውን እንደጠመዱ፤ በጅሮንድ ባልቻም በስተቀኝ በኩል ሌሊቱን ምሽግ ሰርተው መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣልያኖችም የእነሱን መጠጋት ባወቁ ጊዜ ካሰለፉት ከ56 እስከ 64 የሚገመተውን የተወሰነውን የመድፍ እና የጠመንጃ ተኩስ አበረከቱ።
አነጣጥሮ በመተኮስ የተመሰገኑት ሊቀ መኳስ አባተም አባ ይትረፍ በሩቅ በሚያሳየው መነጽራቸው ጣልያኖች ታቦቱን አስወጥተው መድፍ በመትከል የመሸጉበትን ቤተክርስትያን ህንፃ በመመልከታቸው አስተካክለው ቢተኩሱ የመድፉ ጥይት በቤተክርስትያኑ መስኮት ገብቶ የጠላትን መድፍ እግር ሰባበረው።
በዚህ ጅብዳቸውም እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው
“መድፋቸው ተርቦ አፉን ከፍቶ ቢያየው
አባተ አባ ይትረፍ ጥይት አጎረሰው!”
ጣልያኖችም ከተበላሸው መድፋቸው ጭስ እየጨሰ ባዩ ጊዜ በአፀፋው የመድፍ ጥይት ሊቀመኳስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻ ባሉበት ቦታ ላይ እንደ በረዶ አወረዱባቸው፡፡ ነገር ግን አንድም ሰው አልቆሰለም። ይህን ውጊያም አፄ ምኒልክ፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት እና ሌሎችም መኳንንቶች ከድንኳናቸው ወደላይ ካለው ከፍተኛ ስፍራ ላይ ሆነው በመነጽር ሲመለከቱ ነበር።
እቴጌ ጣይቱም የድንኳናቸውን መጋረጃ ገልጠው ሁኔታውን ሲመለከቱ ስለነበር በአቅራቢያቸው ወደነበሩት አዛዥ ዘአማኑኤል ፊታቸውን አዙረው “ሂድ እና ከሊቀ መኳሥ አባተ ጋር እየተመካከርክ የውሀውን ምንጭ ለመያዝ ትችል እንደሆነ ሞክር” በማለት አዘዟቸው።
እሳቸውም ወዲያው በመሄድ እንደታዘዙት ከሊቀ መኳስ አባተ ጋር ቢነጋገሩ ሊቀ መኳሱ “የምንጩ ስፍራ ጥልቅና ወደ ጠላት ምሽግ የቀረበ ነው፡፡ በምንጩ እና በጠላት ምሽግ መካከል አንድ መቶ ሃምሳ ክንድ የሚሆን ርቀት አለ፡፡ ቢሆንም ግን መተላለፊያውን በመድፍ ሳስጠብቅ እቆይና ከዚያ በሌሊት ወታደር ልኬ ምንጩን አስይዛለሁ” ብለው መለሱላቸው።
ሊቀ መኳስ አባተ በምሽግ ያሉትን በጥብቅ እየጠበቁ ወዲያና ወዲህ እየተዘዋወሩ በመድፍ እና በመትረየስ እየመቱ ጠላት ምሽጉን እስኪለቅ ድረስ ለአሥር ቀን ድረስ ሳይተኙ እና ከመሳሪያቸው ሳይለዩ ሰነበቱ።
ሊቀ መኳስ አባተ የሰሩትን ሥራ ማንም ሊሠራው አይችልም። እቴጌ ጣይቱም በየቀኑ ከሌሊቱ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሠዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውሃውን ለሚጠብቁ ወታደሮች መጠጥ የያዘ እንሥራ እና በመሶብ እንጀራ ሥጋ እየጨመሩ ይልኩ ነበረ።
በሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለውን እና በበጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎ የሚመሩት የጦር ወታደሮችም እየበሉ እየጠጡ ሕይወታቸውን ለሀገራቸው እና ለንጉሳቸው ለመሰዋት ሲሉ አንድ ቀንም መሳሪያቸውን ትተው ሳይተኙ ጠላት ውሀ እንዳይወስድ እየተከላከሉ ቆይተው በመጨረሻ ምሽጉን እስከማስለቀቅ ደረሱ።
ጣልያኖች በተከታታይ እየወጡ በመዋጋት ምንጩን ለማስለቀቅ ሞክረው በኛዎቹ ጥብቅ ተከላካይነት ሳይሳካላቸው ስለቀረ ሁሉም ወደ ምሽጋቸው በመሸሽ ተመልሰው ገቡ።
ነገር ግን በእነዚህ ጊዜያት በአንደኛው ሙከራ ሁለት ጊዜ መድፍ ተተኩሶ ነበር፡፡ የአንደኛው መድፍ ጥይት የጣልያኖቹን መድፍ አፍ ገብቶ ሰባበረው። ይህ መድፍ በማይጠረጠር ከሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለው የተተኮሰ መሆን አለበት ተባለ። በዚሁም ምክንያት የሚከተለው ግጥም እንደተገጠመላቸው በገሃድ ተነግሯል።
“አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው፣
የእኛን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው!”
ከድሉ በኋላም ምርኮኛውን እንዲነዱ፤ ምርኮውን እንዲያስጫኑ በአጼ ምኒልክ በታዘዙት መሰረት አዲስ አበባ ድረስ ምርኮኛውን ይዘው የሄዱ አርበኛ ናቸው።
ራስ አባተ አባ ይትረፍ ከተባለው ፈረሳቸው ጋር በጽናት የተዋጉባት አድዋ፤ መድፍ ከመድፍ ያቆላለፉበት የሶሎዳው ተራራ በቅኝ ግዛት ስር ለወደቁ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ጮራና የተስፋ አርአያ ሆና እስካሁን ትኖራለች።
የጦሩ ጀግና የአድዋው ወላፈን በስተርጅናቸው እስር ገጥሟቸው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ግን ሀገራቸውን እስከ ነፍስ ያገለገሉ ተወንጫፊ ረመጥ ነበሩ፡፡
ታላቁ ራስ አባተ ቧ ያለው ንጉሱ ጥር 6 ቀን 1910 ዓ.ም. የተፈጥሮ ሞት ቢሞቱም ስማቸው ግን ከታላቁ ተግባራቸው ጋር ዛሬም ድረስ ህያው ሆኖ ሲነሳ ይኖራል።












