አዲስ አበባ | ታህሳስ 25፤ 2016| NBC ETHIOPIA – በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጉዳይ ለመፈፀም 1 ሚሊየን 4 መቶ ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ ሁለት የመሬት ሊዝ አስተዳደር ፅ/ቤት ሰራተኞች እና ተባባሪያቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቅንጅት ስራ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር የቦታ ርክክብና ክትትል ቡድን መሪ እና የሊዝ ማስተላለፍ ባለሙያ ሲሆኑ ሶስተኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ ለወንጀሉ ተባባሪ የሆነች የሊዝ ማስተላለፍ ባለሙያው እህት ነች፡፡
የግል ተበዳይ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ/ም በሊዝ የገዙትን ቦታ ለመረከብ ሲመላለሱ ከቆዩ በኋላ የግንባታ ማስጀመሪያ ፈቃድ እንዲራዘምላቸው ለመጠየቅ አገልግሎት ፈልገው ነበር ወደ ክፍለ ከተማው አስተዳደር የሄዱት፡፡ ይሁን እንጂ ተጠርጣሪዎቹ ተገቢውን አገልግሎት መስጠጥ ሲጠበቅባቸው ቀጠሮ በማብዛት ሲያመላልሷቸው እንደቆዩ እና ጉዳዩን ለመፈፀም ገንዘብ እንደተጠየቁ ለፖለስ አስረድተዋል፡፡

“በሊዝ የተገዛው ቦታ መንገድ ዳር በመሆኑ እኛ ለምንፈፅምልዎት ጉዳይ የሚከፍሉን ገንዘብ ይጨምራል ” የሚል መደራደሪያ ሃሳብ በማቅረብ ተጠርጣሪዎቹ 3 ሚሊዮን ብር ጠይቀው እንደነበር እና በመጨረሻም ወደ 1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ዝቅ እንደተደረገ የአዲስ አበባ ፖሊስ በዘገባው አስታውቋል፡፡
ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 1 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብሩ የሊዝ ማስተላለፍ ባለሙያው በሆነው ተጠርጣሪ እህት የባንክ ሂሳብ ውስጥ እንዲገባ መደረጉን የጠቀሱት የምርመራ ሃላፊው፤ ከግል ተበዳይ በቀረበ አቤቱታ በአዲስ አበባ ፖሊስ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል 200 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበሉ እጅ ከፍን ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት











