አዲስ አበባ | ታህሳስ 25፤ 2016| NBC ETHIOPIA – አልኮልን አብዝቶ መውሰድ ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች እንደሚዳርግ ይታወቃል ከነዚህም አንዱና ዋነኛው ከአልኮል ጋር የተያያዘ የጉበት ህመም ነው።

አልኮል ከሰውነታችን ውስጥ የሚወገደው በጉበት አማካኝነት ነው ስለዚህም ለረጅም አመታት አልኮልን መጠጣት ወይንም አልፎ አልፎ ከመጠን ባለፈ መልኩ መውሰድ ለጉበት ህመም ይዳርጋል።

አንድ ሰው አልኮል አብዝቶ ተጠቀመ የምንለው በቀን ለወንድ ከ 3 እና ከዚያ በላይ አልኮል መጠጥ ፣ ለሴት ደግሞ ከ 2 እና ከዚያ በላይ አልኮል መጠጥ የሚወስዱ ከሆነ ነው።

የመጠጥ መጠን እንደ መጠጡ አይነትና በውስጡ እንዳለው የአልኮል መጠን ይለያያል ። ለምሳሌ 1 መጠጥ ማለት አንድ ቢራ ፣ 1 ብርጭቆ ወይን ፣ እንዲሁም 1 መለኪያ ከባድ አልኮል (80% spirit) ማለት ሲሆን ሁሉም የመጠጥ አይነቶች በተመሳሳይ መልኩ 14 ግራም የአልኮል መጠን አላቸው።
አልኮል የጉበት ህመምን የሚያስከትልበት ምክንያት በዋናነት በጉበት ሴሎች ውስጥ ስለሚወገድ ነው። አልኮልን በማስወገድ ሂደት ውስጥ acetaldehyde የምንለው ኬሚካል ይፈጠራል ። ይህ ኬሚካል በጉበት ሴሎች ላይ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ ጉዳት ያደርሳል፤ በዋነኝነት በእነዚህ ሴሎች ውስጥ ከፍተኛ የስብ መጠን እንዲጠራቀም በማድረግ የጉበት ላይ የስብ ክምችትን (fatty liver) በመፍጠር ነው። በተጨማሪም በሰውነታችን ውስጥ ያለው የስብ መጠን በአልኮል ምክንያት ይጨምራል ። ይህም በጉበት ላይ ለሚጠራቀመው ስብ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል።
ከአልኮል ጋር የተያያዘ የጉበት ህመም እንዲፈጠር የሚያደርጉ አጋላጭ ሁኔታዎች

1. ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥን መውሰድ
2. ያለምግብ አልኮል መውሰድ
3. ሲጋራ ማጨስ
4. የታወቀ የጉበት ህመም
5. ከመጠን ያለፈ ውፍረት (obesity)
6. እንዲሁም ሴቶች በትንሽ የአልኮል መጠን የጉበት ላይ ስብ የማከማቸት አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከወንዶች ይልቅ ተጋላጭ ናቸው።
የጉበት ህመም ምልክቶች

በአብዛኛው ጊዜ የጉበት ላይ ስብ ክምችት እንዲሁም የመጀመሪያው መጠነኛ የጉበት ጉዳት ምልክት አያሳይም። ስለዚህ የህመም ስሜት ሲመጣ ከፍተኛ የጉበት ጉዳት ደርሷል ማለት ይቻላል።
1.ከፍተኛ የድካም ስሜት
2. መክሳት እና ክብደት መቀነስ
3. የሆድ ህመም ፣የሆድ እብጠት
4. የእግር እብጠት
5. የአይን ቢጫ መሆን
6. የእጅ መዳፍ መቅላት እንዲሁም የመዳፍ ጡንቻ መቀነስ
7. ለወንዶች የፊት ገፅታ እና የቆዳ ቀለም መቀየር
8. ለሴቶች የጡት መጠን መጨመር ፣ የወር አበባ መዛባት
እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል በመሄድ የጉበት ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












