አዲስ አበባ | ታህሳስ 23፤ 2016| NBC ETHIOPIA – የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፓርትና ሎጀክቲክስ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የባህር በር ተጠቃሚ እንድትሆን የተፈረመውን ስምምነት አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ስምምነቱ ለዘመናት የተቆለፈውን በር የሚከፍት ነው ብለዋል።
ወደብ የሌለው ሀገር በር የተቆለፈበት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ስምምነቱ የኢትዮጵያን ተሰሚነት የሚያሳድግ ትልቅ ብስራት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ድሉ በትልቅ ዲፕሎማሲ የተገኘ መሆኑ ደግሞ ትልቅ ስኬት ነው ያሉም ሲሆን፥ የኢትዮጵያን የንግድ ወጪ በእጅጉ የሚቀንስና ንግድን የሚያሳድግ ነውም ብለዋል ዶክተር በሪሶ።
እንደ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፓርትና ሎጀክቲክስ አገልግሎት፥ ተመራጭ የሎጀክቲክስ ተቋም ለመገንባት፣ የመርከብ ብዛትን ለማሳደግና የሰው ሀይል አቅምን ለማጎልበትም ስምምነቱ ትልቅ እድል እንደሆነም ተነስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ባሂ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር በር ለማግኘት እና ለማልማት የሚያስችላትን አካታች የሆነውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ በትላንትናው እለት መፈራረማቸው ይታወቃል:: ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ በሊዝ የወደብ ባለቤት መሆን እንድትችል አድርጓታል።
በሰላማዊት ወንድወሰን
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












