አዲስ አበባ | ታህሳስ 11 ፤ 2016 – ኢትዮጵያ 37ኛውን የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ከየካቲት 14- 18/2016 ታስተናግዳለች፡፡ ለጉባኤው እየተደረጉ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሁኔታዎችን በተመለከተ በቱሪዝም ሚኒስቴር በተዘጋጀ መርሃ-ግብር ላይ የተለያዩ ተቋማት ተገኝተዉ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ለ37ኛ ጊዜ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሚሰጡ አገለግሎቶች የሃገር ገጽታን የሚገነቡ እንዲሆኑ የሆቴል ባለቤቶችንና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጠይቋል።
ሆቴሎች፣አስጎብኚ ድርጅቶች፤ አስጎብኚ ባለሙያዎች እና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት ደረጃን በተመለከተ እያደረጉ ስላሉት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ለመድረኩ አካፍለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ስለሺ ግርማ በወቅቱ እንደገለፁት ፤ የሚሰጠው እያንዳንዱ አገልግሎት የሃገሪቱን ባህልና እሴቶች እንዲሁም እንግዳ ተቀባይነት በሚያንፀባርቅ መልኩ ሊሆን ይገባል ።
ባለፉት ዓመታት ጉባኤው ሲካሄድ የሚስተዋሉት የሆቴሎች የአገለግሎት ጥራት ማነስና የዋጋ ንረት ችግር ሊስተካከል ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅም ከደህንነት ጀምሮ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ አካል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ።
በአስናቀች መላኩ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebbok – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












