አዲስ አበባ | ህዳር 13፤ 2016| NBC ETHIOPIA- የማንኮራፋት ችግር ማህበራዊ ጫና ከመፍጠሩ ባሻገር ጤና ላይ የሚያመጣዉ መዘዝ የጎላ ነው።

የማንኮራፋት ችግር የሚከሰተዉ አየር ከሳንባ ወይም ወደ ሳንባ በሚወጣበት እና በሚገባበት ጊዜ በሚያልፍባቸው የአየር ቱቦ በቂ የሆነ ክፍተት ካላገኘ ወይም የሚያልፍበትን የተመቻቸ መስመር የሚያስቀይር ችግር ካጋጠመው የሚፈጥረው የተዛባ ድምጽ ነው።
ይህን የማንኮራፋት ችግር የሚያስከትሉ ምክንያቶች በህፃናት እና አዋቂዎች ላይ የተለያዩ ቢሆኑም የሚከሠቱበትን ቦታ በ 4 ከፍሎ ማየት ይቻላል፡-

- – ከአፍንጫ እስከ ላንቃ ያለው የአየር መተላለፊያ ሲሆን ህፃናት ላይ በአብዛኛው አዴኖይድ የሚባለው የቶንሲል ክፍል መጠን መጨመርና በአፍንጫ የሚያልፈውን አየር ሲዘጋ የሚከሠት ነው።
– አዋቂዎች ላይ ከዚህ ቦታ በሚነሳ ችግር ማንኮራፋት ከተከሰተ ካንሠርን ጨምሮ ሌሎች እብጠቶችን ማሰብ እና ምርመራ ማድረግ ግድ ይላል።
2. ከምላስ የኋለኛው ክፍል እና በጎኑ ከሚገኙ ቶንሲሎች ጋር ተያይዞ የሚከሰት ማንኮራፋት ነው።

የዚህ ከምላስ ጎን የሚገኘው ቶንሲል የማንኮራፋት ችግር ከመፍጠሩ በላይ በ ተደጋጋሚ የቫይረስ እና የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በመፍጠር ተጨማር የጤና እክል ያስከትላል።
3. በአፍና መንገጭላ አካባቢ የሚከሰቱ የአፈጣጠር ችግሮች እንዲሁም ከነዚህ ቦታዎች ተነስተው የኋለኛውን የአየር መተላላፊያ ሊዘጉ የሚችሉ እብጠቶች እንደ ምከንያት ይጠቀሳሉ።
4. የኋለኛው የአየርና የምግብ የጋራ መተላለፊያ ግድግዳን የሚሠሩ ጡንቻዎች መዛል ፣ በስብ መሞላት ፣ በእብጠት መጠቃት ወይም መግል መቋጠር ከተፈጠረ የሚከሰት ይሆናል።
ማንኮራፍት የሚከሰትባቸውን ምክንያቶች መጠን ከሰው ሰው እንደተፈጠረው የአየር መተላለፊያ መስመር መጥበብ ይለያያል። ይህም ከልማዳዊ ማንኮራፋት እስከ ሳንባ ከረጢቶች መጠን መቀነስ ብሎም የሳንባ ደም ስሮች ግፊት እና የልብ ችግር ሊፈጥር ይችላል።
በተጨማሪም አካላዊና አእምሯዊ የእድገት ችግር ፣ የጸባይ ችግር (በተለይም ህናት ላይ) ፣ ቀን አብዝቶ የመተኛት ችግር ፣ በስራ የመዛልና ውጤታማ ያለመሆን እና የመሳሰሉ ተጽኖዎችን ይፈጥራል።

መፍትሔው የሚወሰነው ማንኮራፋቱ በፈጠረው ችግር እና የችግሩ መጠን ነው

1. በአብዛኞች ህፃናት ላይ ከአፍንጫ ጀርባ እና ከምላስ ጎን ያለውን ቶንሲል በሰርጀሪ በማስወገድ የሚስተካከል ይሆናል።
2. በአዋቂዎች ደግሞ እባጮች (እጢወች) እንደሌሉ ከተረጋገጠ በኋላ ክብደት መቀነስ ፣ የኦክስጅን ህክምና (CPAP) ብሎም የአየር መተላለፊያን ቱቦ ለማስፍት የሚደረጉ ሠርጀሪዎች የህክምና አማራጮች ናቸው።
ስለሆነም ማንኮራፋትን እንደ ቀላል ችግር በማየት አንዘናጋ፤ቢያንስ ያለንበት የማንኮራፋት ደረጃ በምን መስተካከል እንደሚችል ሀኪሞችን ማማከር ያስፈልገናል።











