አዲስ አበባ | ጥቅምት 29 2016| NBC ETHIOPIA – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በ3ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያቀረበውን የ2016 በጀት አመት የአራት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አዳምጧል።

ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ ኘሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራቶቹን በአራት ምዕራፎች ከፍሎ እየሰራ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራቶቹን ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል::
በሂደቱም በአራት ወራት አፈፃፀሙ በአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ ተቋማትን ጨምሮ ተባባሪ አካላት በመለየት ስልጠና መሰጠቱንና እነዚህም ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ያለውን የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ አካታችና አሳታፊ በማድረግ ሂደት ከኮሚሽኑ ጋር አብረው የሚሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን የአጀንዳ መረጣ ስራው እንደተጠናቀቀ ወደ ተግባር ምዕራፍ የሚገባ መሆኑን እና ሕዝቡ በከፍተኛ ናፍቆት የሚጠብቀው ተግባር መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የተሳታፊዎችን ልየታ ስራ በተቀመጠው ፕሮግራም መሰረት ለማከናወን ወቅታዊው የጸጥታ ችግር እና የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስተባባሪዎች ምደባ ላይ ግልጽ አቅጣጫ አለመቀመጥ እንቅፋት እንደሆነባቸው የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ በክልሎች ያለውን የተሳታፊዎች መረጣና የአጀንዳ ልየታ በማጠናቀቅ አሳታፊና አካታች ሀገራዊ ምክክር ማስጀመር የቀጣይ ትኩረት አቅጫዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና የሀገራችንን ፈውስ የሚያረጋግጥ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












