አዲስ አበባ | ጥቅምት 27፤ 2016| NBC ETHIOPIA -በፕሮፌሰር ጎንግ ዌቢን የተመራው የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ የልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት ከተከበሩ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋር የሁለቱን ሀገራት አጋርነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ እና ቻይና በተለያዩ መስኮች አብሮ በመስራት የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በአሁኑ ጊዜ የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ በአስተዳደር ስልጠና እንዲሁም በጥናትና ምርምር ያለውን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ያለውን ዝግጅት አድንቀዋል፡፡
አካዳሚው በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አቅም ያለውና የበርካታ ምሁራን ስብስብ በመሆኑ፤ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተዛማጅ የሆነ ልምድ በማጋራት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር እንደሚገባ አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል፡፡

የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጎንግ ዌቢን ቻይና ከኢትዮጵያም ሆነ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ አካዳሚው በስልጠናም ሆነ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የቻይና ብሄራዊ የአስተዳደር አካዳሚ እና የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ በቅርቡ የሚፈራረሙት የትብብር ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር የተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዩች ም/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram –https://t.me/nbcethiopiatv