አዲስ አበባ | መስከረም 18 2016| NBC ETHIOPIA – በሰሜናዊ ኢራቅ በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸውን እና ሌሎች 150 እንደተጎዱ ታውቋል::

ለእሳቱ አደጋ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ አንዳንድ ዘገባዎች ግን ርችት መተኮሱን ተከትሎ አደጋው እንደተከሰተ አመልክተዋል።
እስካሁን ሙሽሮቹ ከሞቱት ወይም ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ስለመሆናቸው የታወቀ ነገር የለም።
ቀድመው የወጡ ዘገባዎች ሙሽሮቹ በአደጋው ሞተዋል ቢሉም፣ አንዳንድ ዘገባዋች ሙሽሮቹ ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከአደጋው ስፍራ የወጡ ፎቶግራፎች የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ እና በእሳት የተቃጠሉ የሰዎች አስከሬኖችን አሳይተዋል።
የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደበት ሕንጻ የተገናባበት ተቀጣጣይ ነገሮች እሳቱ በቀላሉ እንዲስፋፋ እና ለበርካታ ሰዎች ሞት እና ጉዳት ምክንያት ሳይሆን እዳልቀረ የኢራቅ ባለሥልጣናት መናገራቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
የዐይን እማኞች እንዳሉት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ እየተካሄደ ሳለ በሀገሪቱ የሠዓት አቆጣጠር ምሽት 4፡45 ላይ ነበር አደጋው የተቀሰቀሰው።
አደጋውን ተከትሎ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እና የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው መሰማራታቸውን ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር “በድንገተኛው አደጋ የተጎዱትን ለመርዳት አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንዲደረግ” ማዘዛቸውን ጽህፈት ቤታቸው በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook- https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












