በአዲስ አበባ | መስከረም 7 2016| NBC ETHIOPIA- የስኳር ህመም ከቋሚ ህመሞች መካከል አንዱና ዋነኛው ሲሆን፤ የኢንሱሊን ሆርሞን እጥረት ወይም በትክክል አለመስራት ምክንያት የሚከሰት ህመም ሲሆን የአይን ፣ የኩላሊት ፣የልብና የነርቭ ችግሮች የሚያስከትል ህመም ነው።ስኳር በአራት ዋና ዋና አይነቶች ያሉት ሲሆን የእርግዝና ወቅት ስኳር አራተኛው አይነት ስኳር በመባል ይታወቃል።

✨ የእርግዝና ወቅት ስኳር (GDM) ምንድነው?

የእርግዝና ወቅት ስኳር በእርግዝና ሰዓት የሚከሰት የስኳር ዓይነት ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝና ወቅት የምርመራ የሚገኝ ነው። በአብዛኛው ከ28 ሳምንት እስከ ወሊድ ብሎም ስድስት ሳምንት ድህረወሊድ ድረስ ይቆያል።
በእርግዝና ሰዓት ከሚያጋጥመው የስኳር አይነቶች 90% የሚሆነው የስኳር ዓይነት ከእርግዝና በኋላ የሚጠፋ ዓይነት ነው።
በአብዛኛው የሚታዩ ምልክቶች ባይኖሩትም ከፍተኛ ተጋላጭነት ካለ በምርመራ ሊታወቅ ይችላል።
⚡️ምልክቶቹስ?
• የውሃ ጥም
• የሽንት መብዛት
• የምግብ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር
• የልጅ መፋፋት
• የእንሽርት ውሀ መብዛት
• የፅንስ ያፈጣጠር ችግር
????አጋላጭ ሁነቶች (risk factors)

• የቤተሰብ የስኳር ህመም
• ያለቅጥ ውፍረት
• የበፊት እርግዝና ስኳር
• የደም ግፊት
• የኮሌስትሮል መብዛት
• በእርግዝና ወቅት ያላግባብ ክብደት መጨመር እና ወዘተ…
⛄️እንዴት ይታወቃል?

ሃኪሞችሽ አጋላጭ ሁነቶችሽ ካዪ በኋላ ከ24-28 ሳምንት የስኳር ምርመራ ያደርጋሉ። ይህም ጣፋጭ ስኳር (40% glucose) በአፍሽ ከወሰድሽ በኋላ በየአንድ ሰዓት ልዪነት የደም ስኳር መጠንሽ በመለካት የእርግዝና ስኳር እንዳለ እና እንደሌለ ይናገራሉ። በሌላ የምርመራ ዘዴ (HgA1C) በመመርመርም ማወቅ ይቻላል።
ባደጉ ሀገራት ማንኛውም ነፍሰጡር እናት ለስኳር ምርመራና ልየታ የምታደርግ ሲሆን በታዳጊ አገራት የተወሰኑ ነፍሰጡሮች አጋላጭ ባህሪያቸው ታይቶ የሚመረመር ይሆናል።
????ምክንያቱ ምንድነው?
• የእርግዝና ወቅት ስኳር ለምን እንደሚከሰት በትክክል ምክኝያቱ ባይታወቅም ብዙ ሳይንሳዊ መላምቶች አሉ።
• የሆርሞን አለመመጣጠን በእርግዝና ወቅት የእንግዴ ልጅ እጅግ በጣም ብዙ ሆርሞኖችን የሚያመነጭ ሲሆን ከእነዚህም PLG (plasental lactogen )አንዱ ነው። ይህም ሆርሞን ኢንሱሊን በህዋሳት ወስጥ እንዳይሰራ በማደናቀፍ የደም ውስጥ ስኳር እንዲጨምር ያደርጋል። ስቴሮይድ ሆርሞን እና የእድገት ሆርሞን እንደዚሁ በተመሳሳይ የኢንሱሊን ስራን በማስተጓጎል እንደ ምክንያት ይነሳሉ።
• አካባቢያዊ ተፅኖ በእርግዝና ወቅት የክብደት መጨመር ህዋሳቶች ለኢንሱሊን ሆርሞን እንዳይታዘዙ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሌላ መላምትም አለ።
????????♀️ለመጀመሪያ ጊዜ በርግዝና ወቅት የታወቀ ስኳር የቆየ መሆኑ አለመሆኑ እንዴት ይታወቃል?

• ከሃያ ሳምንት በፊት የተከሰተ ስኳር
• HgA1C ከ7% በላይ ከሆነ
• የረጅም ጊዜ የስኳር ህመም ውስብስ ችግሮች ካሉ ለምሳሌ የዓይን ችግሮች ፣ የኩላሊት ህመም የመሳሰሉት
• የልጅ የአፈጣጠር ችግር ካለ
የቆየ ስኳር አመላካቾች ስለሆኑ በድህረ ወሊድ ጊዜ በድጋሚ ክትትል ያሻል።
????ውስብስብ ችግሮች
የእርግዝና ወቅት ስኳር በእናትና በፅንስ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል
እናት ላይ
• ፅንሱ በመመፋፋቱ ምክንያት ለኦፕራሲዮንና ለመሳሪያ ወሊድ መጋለጥ
• የምጥ መርዘም
• ለልብ ችግር ተጋላጭነት መጨመር
• በወሊድ ወቅት ደም መፍሰስ
• የእንግዴ ልጅ መቅደም ፅንሱ ላይ
• የፅንስ መፋፋት
• ያለጊዜ መወለድ እና የአተነፋፈስ ችግር
• የስኳር ማነስ (hypoglycemia)
• የፅንስ መታፈን
• ሆድውስጥ መጥፋት
• ተደጋጋሚ ውርጃ
• የጨቅላ ቢጫነት
• የጨቅላ ሙቅት መውረድ (hypothermia)
???? ህክምናውስ?

• የአኗኗር ዘዬ መቀየቀር ፦ ማለትም በእርግዝና ወቅት የሚፈቀዱ መጠነኛ እንቅስቃሴዎችን መድረግ፣ ጣፋጭ ምግቦችን በመተው አልያም በመቀነስ የደም ስኳርን መቆጣጠር ይቻላል።
• መድሃኒት፦ የአኗኗር ዘዴ በመቀየር ካልተስተካከለ ወይም በሃኪምሽ ከታመነበት መርፌ (insulin) ወይም ኪኒን (oral hypoglycemic agent) በመጠቀም የደም ስኳርን ማስተካከል ይቻላል።
• የስኳር ህመም ውስብስብ ጉዳቶች እንዳይከሰቱ ቁርስ ከመብላትሽ በፊትና በማንኛውም ጊዜ ምግብ ከበላሽ ከሁለት ሰዓት በኋላ የስኳር መጠንሽን መለካት አትርሺ
• መለካት ብቻ በቂ ስላልሆነ የለካሽውን በመመዝገብ በክትትልሽ ወቅት ለሃኪሞችሽ በማሳየት የመድሃኒትሽ መጠን ለማስተካከል ይረዳል።
• ከፍተኛ የስኳር መጠን ካለሽ ደግሞ ሆስፒታል ተኝተሽ ጥብቅ የፅንስ ክትትል እና የስኳር ልኬት ሊደረግልሽ ይችላል።
☔️????እንዴት መከላከል ይቻላል?
አጋላጭ ሁነቶችን በመቀየር ማለትም ከእርግዝና በፊት ክብደት ማስተካከል፣ ጤነኛ የአኗኗር ዘዴን መከተል ፣ ስፓርት እንቅስቃሴ መስራት ፣ ጭንቀት ማስወገድ ፣ አደገኛ አመጋገብ በማስቀረት (ጣፋጭ ፣ አልኮል፣ ጮማ እና ጨው) በመተው ፣ በቂ ውሃ በመጠጣት እና በቂ እረፍት በማድረግ) ስኳር እና ሌሎች ቋሚ ህመሞችን መከላከል ይቻላል።
በወቅቱ የእርግዝና ክትትል በማድረግ የስኳር ምርመራ በማድረግ በወቅቱ መታከም።
የወደፊት እጣፈንታውስ?
• የእርግዝና ወቅት ስኳር በአብዛኛው ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ ሲሆን የተወሰነው ግን ወደሁለተኛው የስኳር አይነት ሆኖ ሊቀጥል ይችላል።
• የወደፊት የስኳር ህመም ፣ የደም ግፊት እና የልብ ህመሞች ተጋላጭነትን ይጨምራል።
• የወደፊት የእርግዝና ወቅት ስኳር እና አለቅጥ ውፍረትን ያጋልጣል።
• ስለዚህ ድህረ ወሊድ ከስድስት ሳምንት በኋላ የስኳር መጠን በመለካት እና በየጊዜው በመመርመር ቋሚ የስኳር ህመም እንደሌለሽ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook- https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram -https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












