አዲስ አበባ | ጳጉሜ 6 2015| NBC ETHIOPIA – አብሮነት የትናንት ማንነታችን፣ የዛሬ ህልውናችን፣ የነገ ዕጣፈንታችን ነው! :- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አብሮነት የትናንት ማንነታችን፣ የዛሬ ህልውናችን፣ የነገ ዕጣፈንታችን መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የአንድነት ቀንን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል ሙሉ መልክዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ስለ አብሮነት አዘውትሮ መናገር የሚያስፈልገው ለህልውናችን መቀጠል ዋስትና ስለሚሰጠን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ስንል ሕብረት ፈጥሮ ሀገራችንን ከማንኛውም ስጋት በመጠበቅና በማበልፀግ በሁሉም መስክ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና በፈታኝ ወቅቶችም በጋራ በመቆም ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ ነው፡፡
አብሮነት ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን የሚያፀና፣ ብዝኃነታችንን የጥንካሬያችን ምንጭ የሚያደርግ፣ አንዳችን ለሌላችን በማሰብ ከብረት የጠነከረ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚፈጥር እሳቤ እንዲሁም ተግባር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በደም፤ በኢኮኖሚ፤ በታሪክ፤ በሀይማኖት፤ በስነልቦና፤ በባህል፤ እና በሌሎችም ማህበራዊ እሴቶች የተጋመደ የአንድ ታላቅ ሃገር ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የትናንት ማንነቱ፤ የዛሬ ህልውናው እና የወደፊት ዕጣፈንታው የተሳሰረ በመሆኑ የባህላችን እሴት፣ የአይበገሬነታችን ምንጭ የሆነው አብሮነቱን አጥብቆ መቀጠል አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ መከፋፈልና መለያየት እንደ ሕዝብና ሃገር ከማሳነስ በስተቀር የሚያመጣልን ትርፍና ድል የለውም፡፡
የኢትዮጵያዊን በኅብር ሃገር ገንብብቷል፤ ሕዝቦቿን በአብሮነት ከማንኛውም ባዕድ ወራሪ ለመጠበቅ እና በራሳችን ነፃነት መወሰን እንደምንችል በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አሳይተናል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድነቷ ታፍራ እና ተከብራ እንድትቆይ አባቶቻችን መሥዋዕትነት ሲከፍሉ አብሮነት ለሀገር ህልውና ያለውን ዋጋ በመመዘን ነው፡፡
አዲሱ ትውልድም በሀገሩ አንድነት እና በሕዝቦች አብሮነት ላይ በውስጥ ባንዳዎችም ሆነ በውጭ ጠላቶች የሚሰነዘሩ ማናቸውንም ጥቃትና እና የሚዘረጉ የሴራ ገመዶችን በመረዳት ልክ እንዳባቶቹ ለአብሮነት ቀናዒ መሆን አለበት፡፡ አንድነታችንን ለመድፈር እና አብሮነታችንን በፅንፈኝት አስተሳሰብ ሊሸረሽሩ የሚፈልጉ አካላትን ጆሮ በመንፈግ ልናወግዛቸው ይገባል፡፡
አንድነታችንን በመናድ ሊያዳክሙን የሚፍጨረጨሩ ፅንፈኞችን ተባብረን ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን በማክሰም የሀገራችንን ደህነትና የሕዝቦቿን ሠላም ማረጋገጥ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ አብሮነት የማይጥማቸው ፅንፈኞች ብሔርን ከብሔርን፤ ሃይማቶትን ከሃይማኖት በማጋጨት የቆየ አብሮነታችንን ለመናድ ብዙ ርቀት ቢጓዙም መቼም ቢኾን እንደማይሳካለቸው ልናሳያቸው ይገባል፡፡
ዛሬ የአብሮነት ቀንን ስናከብር ሃገራችን ኢትዮጵያ በኅብር የተገነባችና
በጋራ መሥዋዕትነት ተጠብቃ የቆየች መሆኗን ወደ ኋላ መለስ ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ እጣፈንታችን በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን ይበልጥ በመገንዘብ አብሮነታችንን የሚፈታተኑ ተግባራትና አስተሳሰቦችን ለመታገል ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት እለት መሆን ይኖርበታል፡፡
መልካም የአብሮነት ቀን ይሁንልን!!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook- https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram – https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት