በአዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2015፣ NBC ETHIOPIA-የቫግነር ቡድን አዛዥ የሆነው የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተሳፍሮበት ህይወቱን አጥቶበታል የተባለውን የአውሮፕላን አደጋን በተመለከተ ወዲያውኑ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው የቆዩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዝምታቸውን ሰብረዋል።

ፑቲን በአደጋው ሕይወታቸው ላለፈ ሰዎች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የቫግነር ቡድን መሥራች እና መሪ የነበረውን ፕሪጎዢንን “ባለተሰጥኦ የንግድ ሰው” ሲሉ ገልጸውታል።
ፑቲን በቴሌቪዥን በተላላፈ ንግግራቸው ላይ የአውሮፕላን አደጋውን በተመለከተ ምን እንደተከሰተ ምርመራ እንደሚካሄድ፣ ነገር ግን ጊዜ እንደሚፈልግ አስረድተዋል።
ፑቲን “ፕሪጎዢንን ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ” በማለት በንግግራቸው የነበራቸውን ግንኙነት ጠቅሰው፣ ሌሎችንም ጉዳዮች አንስተዋል።
ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በፕሪጎዢን ተመርቶ የከሸፈውን አመጽ በማመልከትም “ፕሪጎዢን የተወሳሰበ ዕጣ ፈንታ የነበረው፣ በሕይወቱም ከባድ ስህተቶችን የፈጸመ ሰው ነው። ነገር ግን በጠየቅሁት ጊዜ ለእራሱ እና ለእኔም ጠቃሚ ውጤቶችን አስገኝቷል” ብለዋል።
አደጋው በደረሰበት አውሮፕላን ውስጥ ከፕሪጎዢን ጋር ምክትሉ ዲሚትሪ ኡትኪንን ጨምሮ አምስት የቫግነር አባላት እንዲሁም ሦስት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ነበሩ።
በሃና ተሰማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc/












