አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2015 ፣ NBC ETHIOPIA – “አዲስ ቱሞሮ” ፕሮጀክት “የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ሚና የሚያልቅ ፕሮጀክት ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ በ600 ሺህ ካሬ ሜትር “አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና” በጋራ መገንባት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ ዛሬ ተካሄዷል።
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ‘China First Highway Engineering Group’ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ “በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን መገንባት የሚያስችል ነው” ሲሉ ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።
በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና የዚሁ ስራ አካል በሆነው ስምምነት ከቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ጋር በሽርክና ለመስራት ከተማ አስተዳደሩ 35 ሄክታር መሬት በወቅታዊው የሊዝ ዋጋ ተሰልቶ እንዲቀርብ ማድረጉን አመልክተዋል።
ኩባንያው የፋይናንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና ልምድን ይዞ ግንባታውን ያከናውናል ነው ያሉት።
ከንቲባዋ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት አለው ያሉት “አዲስ ቱሞሮ” ፕሮጀክት ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ግንባታው እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የንግድ ዞን፣ የትምህርትና የባህል ዞን፣ የፋይናንስና ቢዝነስ ዞን እንዲሁም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ዞንን የሚያካትት ነው።
“ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እምብርት እና የቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል እንዲሁም የከተማችንን ዓለም አቀፍ ሚና የሚያልቅ ሲሆን ለበርካቶች የስራ እድል የሚፈጥር ታላቅ ፕሮጀክት ነው” ሲሉ ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
ከንቲባ አዳነች ለዚህ ስምምነት መሳካት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በከተማው ነዋሪዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc












