አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 11/2015፣ NBC ETHIOPIA -በቀጣዮቹ 10 ቀናት የሚኖረው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለሰብል በሽታዎች እና ተባዮች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

በአብዛኛዎቹ ክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው አስታውቋል።
የአየር ሁኔታ አዝማሚያ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የሰሜንና የምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጥላል። ይህም በማሳ ላይ ውሃ እንዲተኛ የሚያደርግ በመሆኑ መቀልበሻ ቦዮችን ከወዲሁ መሥራት ያስፈልጋል።
የዝናብ ሰጪ ገጽታዎች ካለፉት አሥር ቀናት በበለጠ ሁኔታ እየተጠናከሩ የሚሄዱ ሲሆን በተጨማሪም አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ለወንዞች ሙላትና ለቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብሏል።
እንደ ኢፕድ ዘገባ ሰሜን ምስራቅ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ መካከለኛውና ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመቀነስ አዝማሚያ ያሳያል ያለው ኢንስቲትዩቱ፤ በሌላ መልኩ በሰሜንና በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች የተነሳ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ።
በተጨማሪም አብዛኛው አባይ፣ ተከዜ፣ የላይኛው እና የመካከለኛው ኦሞጊቤ፣ ባሮአኮቦ፣ የስምጥ ሸለቆ፣ አዋሽ፣ አፋር ደናክል የላይኛው ዋቢ ሸበሌና የገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚያገኙ እንደሚጠበቅ አመላክቷል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc












