አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015 NBC Ethiopia- በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ወታደሮች በብሔራዊው ቴሌቪዥን መፈንቅለ መንግሥት አወጁ።

ሕገ-መንግሥቱን መበተናቸውን፤ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ለጊዜው ሥራ ማቆማቸውን እና የሃገሪቱ ድንበሮች መዘጋታቸውን ይፋ አድርገዋል።
የኒጀር ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም በወታደሮች ቁጥጥር ሥር እንዳሉ ተዘግቧል። ፕሬዝደንት ባዙም በምዕራብ አፍሪካ እስላማዊ ተዋጊዎችን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የምዕራባዊያን አጋር ሲሆኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶተኒ ብሊንከን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ለፕሬዝደንቱ “ድጋፍ እንደምታደርግ” ቃል እንደገቡም ተደምጧል ተያይዙም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፕሬዝደንቱን እንዳገኟቸው ገልጸው ድርጅታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።
የኒጀር ጎረቤት የሆኑት ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ በቅርብ ዓመታት በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ታምሰው እንደነበር አይዘነጋም።
በሁለቱም ሃገራት ወደ ሥልጣን የመጡት ወታደራዊ አስተዳደሮች የቀድሞ ቅኝ ገዥ ከሆነችው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል።
ረቡዕ ዕለት ዘጠኝ የወታደር መለዮ በለበሱ ሰዎች ተከበው በቴሌቪዥን መስኮት መግለጫ የሰጡት ኮሎኔል ሜጀር አማዱ አብድራማኔ “እኛ የመከላከያና የፀጥታ ኃይሎች የምታውቁት መንግሥት ከሥልጣን አውርደናል” ብለዋል።

የሀገሪቱ ሁሉም ተቋማት ለጊዜ ሥራ እንደሚያቆሙ የገለጹት ኮሎኔሉ ሚኒስትሮች የቀን ተቀን ሥራውን እንደሚመሩ ገልጠዋል።
“ሁሉም የውጭ ሀገራት ጣልቃ እንዳይገቡ እንጠይቃለን። ሁኔታዎች እስኪረጋጉ በምድርም ሆነ በአየር ድንበራችንን ዘግተናል” ብለዋል።
አክለውም ላልተወሰነ ጊዜ ከምሽት 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11 የሚቆይ ሰዓት እላፊ መታወጁንም አሳውቀዋል።ወታደሮቹ በቴሌቪዥን ቀርበው ይህን ካሉ በኋላ፤ ብሊንከን ፕሬዝደንት ባዙም እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል።የምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ-ሃብት ጥምረት የሆነው ኤኮዋስ በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት አውግዟል።

የኤኮዋስ ተዋካይ የሆኑት የቤኒኑ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ታሎን ለሽምግልና ወደ ዋና ከተማዋ ኒያሜይ አቅንተዋል።
ረቡዕ ዕለት በዋና ከተማዋ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞች ለፕሬዝደንት ባዙም ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጥ ወጥተዋል።
የቢቢሲ ዘጋቢ እንደተመለከተው ደግሞ የፕሬዝደንቱ ታማኝ የሆኑ ወታደሮች ብሔራዊውን ቴሌቪዥን ታጥቀው ሲጠብቁ ነበር። ምንም እንኳ መፈንቅለ መንግሥት ያሰቡ ወታደሮች ሰልፈኞችን ለመበተን ተኩስ ቢከፍቱም ከተማዋ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ነበረች።
ኒጀር ከማሊና ከናይጄሪያ በሚነሱ እስላማዊ ጂሃዲስቶች ከ2015 ጀምሮ ተወጥራ ቆይታለች። ከአል-ቃይዳና ከኢስላሚክ ስቴት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ኒጀር ውስጥ ሠፍረዋል። የፈረንሳይና የሌሎች ምዕራባዊያን መንግሥት አጋር የሆኑት ፕሬዝደንት ባዙም በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት በ2021 ነው።
በሃና ተሰማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት