
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2015 NBC Ethiopia- በሚቀጥሉት አምስት ቀናት በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ቦታዎች ላይ ከመደበኛ በላይና በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከአየር ሁኔታ ክስተቶችና ትንበያ በመነሳት በመካከለኛው፣ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ነጎድጓዳማ እና በረዶ የቀላቀለ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ መግለጫው ከሆነ፤ አዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል፣ አማራ ክልል፣ ጋምቤላ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ክልል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በአብዛኛው ቦታዎቻቸው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ መሆኑን ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፤ የአፈር መሸርሸርና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ማሳሰቡን ኢ ፕ ድ ዘግቧል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia












