አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 13 2015| NBC Ethiopia- በአዳማ ከተማ አሊ ቢራ አደባባይ ዛሬ ተመርቋል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ለክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ መታሰቢያ የቆመው ሐውልት ትውልዱ ራዕዩን እንዲያስቀጥል የሚማርበት ነው።
“አሊ ቢራ የአንድነት፣ የእኩልነት፣ የነፃነትና የፍቅር አባት ነው” ያሉት አፈ ጉባኤዋ በተለይ አንድነትና ፍቅርን በጥበቡ ያስተማረ የጥበብ አባት መሆኑን ገልጸዋል።
ትውልዱ እንዲሁም አርቲስቶች በህዝቦች አንድነት፣ መቻቻልና አብሮነት ላይ በቅንጅት በመስራት የአርቲስት አሊ ቢራን ራዕይ ማስቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በክልሉም ሆነ በሀገሪቷ አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ ብሎም የህዝቦች አንድነት እንዲፀና መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አፈ ጉባኤዋ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የአሁኑ ትውልድ ከአሊ መልካም ተግባር እንዲማርና ራዕይውን እንዲያስቀጥል በማድረጉ ለከተማዋ ህዝብና መስተደድሩ ምስጋና አቅርበዋል።

“አሊ ቢራ ፍቅር፣ አንድነትና እኩልነት ያቀነቀ የነፃነት አባት ነው ” ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ ናቸው።
“አሊ ለትናንት ትውልድና ስለ ወደፊቱ ትውልድ ሚና አስተማሪ የሆኑ የጥበብ ስራዎችን ለህዝቡ ያበረከተ ነው” ብለዋል።
ትውልዱ እንዲማር፣ ያለትምህርት ዕድገት፣ ልማት፣ አንድነትና ፍቅር የለም በማለት ለአሁኑ ትውልድ ጭምር ስንቅ ያስቀመጠ የጥበብ አባት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአሁኑ ትውልድ አሊ በጀመረው መንገድ የህዝቦች አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር እንዲጎለብት መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው “ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር የዘከረ ታላቅ አርቲስት ነው “ብለዋል።

“የመታሰቢያ ሐውልት ስናቆም አርቲስት አሊ ቢራ በአስቸጋሪ ወቅት ውስጥ ሆኖ የሰራውን ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን ትውልዱ የአርቲስቱን ፈለግ በመከተል ትምህርት እንዲወስድበት ነው” ሲሉ አክለዋል።
የኦሮሞ ህዝብ በቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝ፣ እንዲሁም ከሌሎች ህዝቦች ጋር በአንድነትና በፍቅር እንዲኖር በጥበቡ ያወሳ በመሆኑ ከአርቲስት አሊ ቢራ መማር አለብን ሲሉም አመልክተዋል።
ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የሰራውን ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድና አርቲስቶች ስለ ህዝቦች አንድነት በጥበባቸው መዘከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ሙሐመድ አህመድ ቆቤ በበኩላቸው “ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ህዝብን በማንቃት የነፃነት ድምፅ የሆነ ነው “ብለዋል።
ትውልዱ የአርቲስቱን ራዕይ በማስቀጠል በትምህርትና በዕውቀት የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ከአሊ በመማር መትጋት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደርና ህዝቡ አሊ ቢራን በሆስፒታል ከመንከባከብ ባለፈ በከተማዋ ጎዳና በመሰየምና የመታሰቢያ ሐውልት በማቆም ትውልዱ ከአሊ እንዲማር ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ ” የክቡር
ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ባለቤት ወይዘሮ ሊሊ ማርቆስ ናቸው።
“አሊ ሀገር አለኝ፤ ለሀገሬ በሀገሬ እኖራለው፤ በሀገሬ እሞታለሁ ብሎ ባቀነቀነው ታሪክ ወጣቱ ስለ ሀገር ፍቅር እንዲማር፣ መቻቻልና አብሮነት እንዲጠናከር አድርጓል ” ሲሉ ለባለቤታቸው ክብርና ምስጋናቸውን ችረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia









