አዲስ አበባ | ሐምሌ 12 2015 | NBC ETHIOPIA :-የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ። ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ እና የእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጂዲ ሲንግ (ዶ/ር) ፈርመዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የእስያ አፍሪካ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ወዳጅነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ አቶ አክሊሉ ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የእስያ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ባህልን ለማጠናከር እና በተለይም
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዲያድግ ትልቅ ድርሻ የሚኖረው በመሆኑ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ማስቀጠል ለአገርም ሆነ ለኮርፖሬሽኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
የእስያ አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጂዲ ሲንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመግባቢያ ስምምነቱ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲመጡ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው እና በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት እንደሚሠሩ ነው ያረጋገጡት።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት ካደረጉት ባለሃብቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት የእስያ ባለሃብቶች ሲሆኑ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc









