
አዲስ አበባ |የካቲት 21 2015 | NBC ETHIOPIA- የናይጄሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ውጤት ከሚነገርበት አዳራሽ አቋርጠው ወጡ።
በናይጄሪያ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ተጠናቆ ባያልቅም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ዋነኛ ተቃዋሚዎቹ ፒፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ፒዲፒ) እና ሌበር ፓርቲ አዲሱ የኤሌክትሮኒክ የመራጮች ሥርዓት ላይ ግልጽነት የጎደለው ሁኔታ አይተናል ብለዋል።
በናይጄሪያ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ የመራጮችን ማንነት ለመለየት ጥቅም ላይ ሲውል ይህ የመጀመሪያው ነው።
የናይጄሪያ ምርጫ ኮሚሽን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል።
ኢኔክ የተሰኘው የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ ያኩቡ የምርጫ ውጤቱን የማሳወቁ ሂደት ይቀጥላል ብለዋል።
በአቡጃ በሚገኘው የምርጫ ማዕከል የተገኙት የፒዲፒ ተወካይ ሂደቱ የተጭበረበረ መሆኑን ገልጸው ገዥው ኤፒሲ ፓርቲ ከምርጫ ኮሚሽኑ ጋር ተመሳጥሯል ሲሉ ከሰዋል።
የሌበር ፓርቲ ተወካይ በበኩላቸው የምርጫ ውጤቶች እንዲታገዱ ወይም ተሰርዘው ሌላ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
እስካሁን ባለው የምርጫ ውጤት እየመሩ ያሉት የገዥው ፓርቲ እጩ ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ በበኩላቸው በውጤቱ ያልተደሰቱ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሚችሉ ጠቁመው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሂደቱ እንዲቀጥልና እስከሚጠናቀቅ እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።
ከ36 ግዛቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የምርጫ ውጤቱን አሳውቀዋል። በዚህም መሰረት የገዥው ፓርቲ ቦላ ቱኒቡ 44 በመቶ ድምጽ ያገኙ ሲሆን፣ አቡበከር 33 በመቶ እንዲሁም ኦቢ 18 በመቶ ይዘው ይከተላሉ።
ነገር ግን ውጤቱ ይፋ ያልሆኑ የፒዲፒና የሌበር ፓርቲ ጠንካራ ድጋፍ ያለባቸው የሰሜን እና ደቡብ ምስራቅ ግዛቶች ስፍራዎችን ያላካተተ መሆኑን ተከትሎ የመጨረሻው ውጤት ከአሁኑ በእርግጠኝነት መተንበይ አይቻልም ተብሏል።
በሃና ተሰማ
ምንጭ(ቢቢሲ)
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት