
አዲስ አበባ |የካቲት 13 2015 | NBC ETHIOPIA- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ በመገኘት ድንገተኛ ጉብኝት አደረጉ። ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ከተፈጸመባት ከአንድ አመት በኋላ ፕሬዝዳንት ባይደን ሀገሪቷን ሲጎበኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ወረራ ከጀመረች አንስቶ በርካታ የውጭ አገር መሪዎች ወደ ኪዬቭ በማቅናት ለአገሪቱ አጋርነታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ወደ ኪዬቭ ካቀኑ መሪዎች መካከል የአሁኑ እና የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትሮች ሪሺ ሱናክ እና ቦሪስ ጆንሰን፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሽልዝ ይገኙበታል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ዩክሬን መዲና ከመጓዛቸው በፊት ከጎረቤት አገር ፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድሬዝ ዱዳ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረው ነበር። በኪዬቭ በሚኖራቸው ቆይታ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የጦርነት እቅድ “የተሳሳተ ነው” በማለት ለኪዬቭ 500 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ እና በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጣል ቃል ገብተዋል።
በቅርቡ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በአሜሪካ ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ በተለይ አሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች።
ሃና ተሰማ
ምንጭ(ቢቢሲ፣አልጀዚራ)
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት









