
የአዲስ አበባ |የካቲት 11 2015 | NBC ETHIOPIA- 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መቀላጠፍ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬታማነት የበኩሉን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ።
በጉባኤው ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም እስካሁን በአግባቡ ለመጠቀም አልታደለችም ብለዋል።
አህጉሪቷ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየተፈተነች መሆኗን ጠቅሰው ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
አፍሪካ እውን ለማድረግ የጀመረችው ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር ለአህጉሪቷ እመርታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ዋና ጸሃፊው ገልጸዋል።

በአፍሪካና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች በተለይም ታዳጊ አገራትን በመደገፍ ካሉባቸው ውስብስብ ችግሮች እንዲወጡ መስራት ይገባልም ብለዋል።
የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለአፍሪካና አጠቃላይ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች በሚጠቅም መልኩ መቃኘት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ዓለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር እልባት ለማበጀት የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአረንጓዴ ልማት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠልና በአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ተጎጂ ለሆኑ አገሮችም በዘላቂነት እገዛና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካን የልማት እቅዶች በመደገፍ በአህጉሪቷ ዘላቂ ሰላምና ቀጣይነት ያለው ልማት እውን እንዲሆን ይደግፋል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየተወያየ ያለው 36ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል።
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት