
የአዲስ አበባ |የካቲት 11 2015 | NBC ETHIOPIA-አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቋሚ መቀመጫ እንድትወከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በህብረቱ ጉባኤ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር፤ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ውክልና ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ በላይ ያላት አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታውን ምክር ቤት ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በቂ ውክልና የላትም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቢያንስ አንድ ቋሚ መቀመጫና የተለዋጭ አባላት ቁጥር ካለበት እጥፍ ሊሆን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካውያን በጸጥታው ምክር ቤት፣ በቡድን 20 እና በቡድን 7 አገሮች ድምፃቸውን የሚያሰሙበት በቂ ውክልና እንዲኖራቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጣቸውን የተዛባ እይታ ለማስተካከል የራሳቸውን ታሪክ ነጋሪ የመገናኛ ብዙኃን ማቋቋም ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያት ስንፈልጋችሁ ከጎናችን የነበራችሁ አፍሪካውያንና አጋሮቻችን ላቅ ያለ ምስጋና ይገባችኋል” በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን እሳቤ ግጭትን ከመፍታት ባሻገር የአህጉሪቷን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ መጠቀም ይገባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በንግግራቸው የአፍሪካ ህብረት ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት አህጉሪቷን የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሁንም በርካታ ስራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል ነው ያሉት፡፡
በተለይ ለአፍሪካዊ ችግሮቻችን አፍሪካዊ መፍትሄ በማበጀት በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ያለፈው ዓመት የህብረቱ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ጦርነት ለማስቆም ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ችግሩ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሰላም ተፈቷል፤ ኢትዮጵያም ሰላም ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያም ይህንኑ መርህ በመከተል በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም ለማስፈን በብርቱ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ በዚህ ረገድ አንስተዋል፡፡
መልማት ከሚችለው የአህጉሪቷ መሬት ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነው አሁንም ገና ጥቅም ላይ አለመዋሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ግብርናን ማዘመን ላይ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የክላስተር ግብርናን በማስፋፋት በዘርፉ የተሻለ ስኬት ማስመዝገቧን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ ስንዴ ለወጪ ንግድ ማቅረብ መቻሏን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ምርታማነትን በማሻሻል በአፍሪካ ያለውን የምግብ ፍጆታ እጥረት ለማሻሻል የበኩሏን ለመወጣት እንደምትሰራ አብራርተዋል፡፡
ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ “የሌማት ትሩፋት” የተሰኘና የምግብ ምርቶችን ማስፋት ላይ ትኩረት ያደረገ መርሃ ግብር መጀመሯን ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም አንጻርም ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሏን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር በመላው አፍሪካ እንዲሰፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሃና ተሰማ
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት