
አዲስ አበባ |የካቲት 10 2015 | NBC ETHIOPIA በአፍሪካ እየተባባሰ የመጠው የደኅንነት እጦት ችግር እንዲሁም የምግብ እጥረት ቀውስ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ዋነኛ አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ተገለጸ።
የአፍሪካ ኅብረት የሚኒስትሮች ጉባኤ ቀድሞ የተጀመረ ሲሆን፣ የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ ከነገ ቅዳሜ እና እሁድ የካቲት 11 እና 12/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ሮይተርስ እንደዘገበው በዚህ ጉባዔ ላይ በአህጉሪቱ ያለውን የደኅንነት ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል ገንዘብ ከአሜሪካ፣ ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት እና ከአውሮፓ ኅብረት ለማሰባሰብ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ይደረጋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ አዲሱን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያሰባስቦ ሮይተርስ በዘገባው አክሎዋል።
የአገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ስላለው ግጭት እንዲሁም እ.አ.አ 2021 እና 2022 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በተከናወነባቸው በማሊ፣ በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ እና በሱዳን ስላለው የደኅንነት ሁኔታ ገለጻ እንደሚደረግ ሮይተርስ ገልፃል።
ከደኅንነት ጉዳዮች በተጨማሪ የጉባዔው ተሳታፊዎች በአህጉሪቱ በርካቶችን እየጎዳ ስላለው የምግብ እጥረት ይወያያሉ፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ የድርቅ ስጋት አለ። በተለይ ለአምስት ወቅቶች ዝናብ ያላገኘችው ሶማሊያ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን ከ200 ሺህ በላይ ሶማሊያውያኑ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን እና በረሃብ እየሞቱ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን ይህ አሃዝ ወደ 700ሺህ ከፍ ሊል እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡
ቅዳሜ በሚጀምረው በ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አዲስ አበባ ገቡተዋል፡፡
በውይይቱ ለመሳተፍ ቀድመው አዲስ አበባ ከደረሱ የአገራት መሪዎች መካከል የደቡብ ሱዳን፣ የሩዋንዳ፣ የጊኒ ቢሳዎ፣ የሌሴቶ፣ የሊቢያ፣ የታንዛኒያ፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ እና የኮትዲቯር መሪዎች ይገኙበታል።
ሃና ተሰማ
ምንጭ(ሮይተርስ)
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት