፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 28 2016| NBC ETHIOPIA- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሲያደርገው የነበረውን በረራ ከዛሬ ጀምሮ ማቋረጡን ገልጿል።
አየር መንገዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው አገልግሎቱን ለመስጠት በኤርትራ በኩል ባጋጠመው ከአቅም በላይ የሆነ የአሰራር ችግር ምክንያት እንደሆነ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።
የአየር መንገዱ የአስመራ ቅርንጫፍ የሂሳብ ደብተር ሙሉ በሙሉ መታገዱ ወደ ከተማዋ ያደርገው የነበረው በረራ ለመቋረጡ አንድ ምክንያት መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ ኤርትራ ውስጥ የናቅፋ እና የውጭ ገንዘቦች አካውንት እንዳለው የጠቀሱት አቶ መስፍን፤ ይህን ገንዘቡን በፈለገው ጊዜ የማንቀሳቀስ መብት እንዳለው ገልፀዋል።ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይህን ገንዘቡን እንዳያንቀሳቅስ በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መከልከሉን ጠቅሰዋል።
በዚህም አየር መንገዱ ገንዘቡን ማንቀሳቀስ እና ለተለያዩ ወጪዎች መጠቀም ባለመቻሉ በረራውን ለማቋረጥ መገደዱን አስታውቀዋል።እንዲያም ሆኖ ያጋጠሙ ችግሮችን በአፋጣኝ በንግግር ለመፍታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም ዝግጁ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ጣሰው መግለፃቸውን ኢቢስ ዘግቧል፡፡












