፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 09 2016| NBC ETHIOPIA-የአየር ንብረት በነፍሰ-ጡር እናቶች ላይ ተፅዕኖ እየጎላ መምጣቱን ያስነበበው ቢቢሲ በተለይ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን በእርግዝና ወቅት በጽንስ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት አደገኛ ነው ይላል፡፡ ይህም የነብሰ-ጡር እናቶችን ህይወት በአስጊ ሁኔታ ላይ እንዲቆይ አድርጓል፡፡
ቢቢሲ በሰራው ዘገባ በጋምቢያ ኬኔባ በምትሰኘው የገጠር መንደር ላይ ያለን የእናቶች ስቃይ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡ ኤድሪሳ ሲንጃንካ በመንደሩ በአዋላጅነት እየሰራ የሚገኝ ሀኪም ነው፣ እርሱ ነፍሰጡር እናቶችን ማገዝ ያስ ደስተኛል ይላል፡፡ ነገር ግን እናቶች ወደ እኔ ሲመጡ ከንፈራቸው ደርቆ እና ተሰንጥቆ ፤ራስ ምታት በከፍተኛ መጠን ሲፈትናቸው ማየቴ የተለመደ ነው ይላል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሙቀት መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ በነብሰ-ጡር እናቶች ላይ እያጋጠመ ያለውን የጤና እክልን ይናገራል፣ እርሱ እንደሚለው እናቶች የእርግዝና ወቅታቸው አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ አንዳንድ ሴቶች በምጥ ወቅት እየተቸገሩም ነው፡፡በወሊድ ምክንያት ህይወታወቸውን የሚያጡ እናቶች እየተበራከቱ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

በጋምቢያ የታየው ሙቀት መጨመር በዚች የገጠር መንደር የሚገኙ እናቶች በእርግዝና ወቅት ከፍተኛ ስጋት እንዲደቀንባቸው አድርጓል፡፡በኬኔባ አካባቢ 92 ነፍሰ-ጡር እናቶች ላይ በተሰራ ጥናት የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ በየሁለት ወሩ አንድ ጊዜ በሚከሰት የሙቀት መጠን መጨናነቅ ታይቶባቸዋል፡፡
ከመደበኛ በላይ የሆነው የሙቀት መጠን ጭንቀት፣ የልብ ምት መጨመር እንዲሁም የእንግዴ ልጅ የደም መፍሰስ መጠን በ17 በመቶ ጭማሪ እንዲያሳይ አድርጓል፡፡ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑእናቶች በዚህ ችግር ውስጥ መሆናቸው መረጃው ያመላክታል፡፡በጋምቢያ፣ የሙቀት መጠኑ ከ45C ተሻግሯል፡፡
በተለይ ከ2023 ጀምሮ ዓለምን እያስጨነቀ የመጣው የዓለም ሙቀት መጠን መቆጣጠር ላይ ካልተሰራ በህጻናት፣ አዛውንቶች ፣ እና ስር በሰደደ የጤና ችግር ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ብሎም ነፍሰጡሩ እናቶች ላይ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡
በእርግዝና ወቅት የሆርሞን ለውጦች እና የቆዳው መለጠጥ ወይም መስፋት እናቶች ይበልጥ ለሙቀት ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
በሙቀት የተፈተኑ ነፍሰጡር እናቶች የመውለጃ ቀናቸው ሲቃረብ ለልብ ሕመም፣ ለደም ግፊት፤ ለስኳር በሽታ እንዲሁም እስከ ሞት የሚያደርስ ስጋት ተደቅኖባቸዋል፡፡ችግሩን ለመቋቋም ቀለል ያሉ አልባሳትን መጠቀም ፣የአካል፣ የስሜት እና ማህበራዊ ጫናዎች ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ መቀነስ፤ ጤናማ አመጋገብ እንዲከተሉ ማድረግ ማለትም ፍራፍሬና አትክልት ማዘውተር፤ በቂ ውሃን መጠጣት፣ የአየር ማቀዝቀዣ መጠቀም፣ የሰውነት እብጠት እንዳይፈጠር ማድረግ እንዲሁም በእርግዝና ወቅት የሚመከሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማከናወን እንደመፍትሄ የሚቀመጡ ናቸው፡፡
በርካታ ሀገራት የሙቀት መጠን መጨመር የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ቢሰሩም ለነፍሰጡር እናቶች የሚደረጉት ድጋፍ አናሳ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ቃል ከገቡ 119 ሀገራት 20 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የእናቶችን እና የፅንስ ጤናን በተመለከተ በእቅዳቸው ማስቀመጣቸውን የተባበሩት መንግስታት የስነ-ተዋልዶ ጤና መረጃ አረጋግጧል፡፡
ጭራሽ ደግሞ በአፍሪካ የሚገኙ እናቶች በከባድ የመተዳደሪያ ስራዎች የተሰማሩ መሆናቸው እና ከሙቀት መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ ችግሩን ለመዋጋት አዳጋች እንዳደረገው ይነሳል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በሙቀት መጨመር በፈረንጆቹ 2024 ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ህፃናት 16 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ይላል፡፡ከፍተኛ የፅንስ መጨንገፍ እና ከወሊድ ጋር የተገናኘ የሞት አደጋም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

ነፍሰ-ጡር እናቶች በተለይ በአፍሪካ የሙቀት መጨመር ለሚፈጥረው ጭንቀት ተጋላጭ ሲሆኑ ችግሩን ለመቋቋም አዳጋች የሚያደርገው እናቶች በከባድ ስራዎች ተሳታፊ መሆናቸው ነው፡፡ስለዚህም የትዳር አጋሮቻቸውን ጨምሮ በዙሪያቸው የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጫናቸውን ሊያቃልሉ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
የሙቀት መጨመር በፅንስ እድገት እና አዲስ በሚወለዱ ህፃናት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በጋምቢያ የተሰራው ጥናት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
በበለጸጉ ሀገራት ነፍሰ-ጡሩ እናቶች ለሙቀት ተጋላጭ ቢሆኑም የህክማናን ክትትል በማድረግ እና ተገቢውን እንክብካቤ ስለሚደረግላቸው የተሻለ ውጤት እንዳለው ይነገራል፡፡ የዓለም ሙቀት መጨመር በነፍሰጥሮች ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል ባለመሆኑ ይበልጥ አትኩሮት ይስፈልጋል ይላል ቢቢሲ፡፡












