ባሳለፍነው የፈረንጆቹ መጋቢት ዓለማችን የተለያዩ ሁነቶችን አስተናግዳ አልፋለች፡፡ ከእነኚህ አበይት ክስተቶች መካከል የተወሰኑትን እንንገራችሁ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስድስት ወራት ሊደፍን ቀናት በቀሩት የእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያሳለፈው ውሳኔ ሌላኛው የወሩ ዓለም ዓቀፍ ትኩረትን የወሰደ ጉዳይ ነበር፡፡

ጦርነቱ በጥቅምት ወር ከጀመረ ወዲህ ከበርካታ የከሸፈ ሙከራዎች በኋላ ምክር ቤቱ የተኩስ አቁም ጥሪ ሲያቀርብ የመጀመሪያው ነው። 14 አባላት ድጋፋቸውን ባሳዩበት ውሳኔ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላት አሜሪካ እርምጃውን አልተቃወመችም፡፡ ውሳኔው ያስቆጣት እስራኤል ደግሞ ተቃውማዋለች፡፡ የእስራኤል ባስልጣናት የአሜሪካ ተግባር ባይደን የእስራኤልን ጠላቶች በዘዴ እንደሚደግፉ ማሳያ ነው ብለውታል፡፡
ይህንን ተከትሎ እስራኤል ልዑካኗ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በዋሽንግተን ሊያደርጉት የነበረውን ስብሰባ ሰርዛም ነበር፡፡ ስብሰባው በራፋ ሰላለው ሁኔታ አማራጮችን ለመፈለግ የሚያስችል ውይይት የሚደረግበት ነበር ያለችው አሜሪካ በእስራኤል ድርጊት መበሳጨቷን ገልጻለች።
የፀጥታው ምክር ቤት በሁለቱም ወገኖች በኩል ያሉ ታጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ቢጠይቅም ቴላቪቭ የታገቱ ዜጎቿ ነጻ ባልወጡበት ሁኔታ በጋዛ ያለውን ጦርነት እንደማታቆም በመከላከያ ሚንስትሯ አማካኝነት አስታውቃለች፡፡
የ144 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውና ከ150 የሚልቁ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው በሩሲያ መዲና ሞስኮ በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ የተሰነዘረው የሽብር ጥቃት ሌላኛው የመገናኛ ብዙሀን ቀዳሚ ጉዳይ ነበር፡፡ 6200 ሰዎችን በሚይዘው የክሮከስ ሲቲ አዳራሽ እየተከናወነ በነበረ የሙዚቃ ድግስ ላይ ነበር አራት ታጣቂዎች ጥቃት ያደረሱት፡፡

ከጥቃቱ ጀርባ ያሉትን እንደምታድን በፕሬዝዳንቷ አማካኝነት የዛተችው ሩሲያ በጥቃቱ ዩክሬንን ተጠያቂ ብታደርግም የአይኤስ አይኤስ የሽብር ቡድን ቅርንጫፍ መሆኑ የሚነገረው አይኤስ-ኬ የሽብር ቡድን ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ ዩክሬን በበኩሏ በጥቃቱ ተሳትፎ የለኝም ስትል አስተባብላለች።
ሀገሪቱ በጥቃቱ ተሳታፊ ናቸው ያለቻቸውን ዘጠኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውላ ምርመራ እያደረገች ነው፡፡ ጥቃት አድራሾቹ በዩክሬን የሚረዱ ናቸው ያለችው ሩሲያ ወደ ዩክሬን ድንበር ለማቋረጥ ሲዘጋጁ በብራያንስክ ክልል መያዛቸውን ገልጻለች፡፡
ከሁለት አስርት አመታት ወዲህ ሩሲያ ውስጥ የተከሰተ እጅግ ከባዱ ነው የተባለው በርካታ ዜጎቿን የነጠቃት ሩሲያ ብሔራዊ የሀዘን ቀን አውጃም ሰንብታለች፡፡
767 ቀኑን ባስቆጠረው የሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት፣ ሩስያ በኦዴሳ ክልል የኤሌክትክ መሰረተ ልማት ላይ ባደረሰችው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በመቶዎ ሺ የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ጨለማ ውጧቸዋል፡፡ የጥይት ሰለባ የሚሆኑ ዜጎች መበራከት ቀውሱን የከፋ አድርጎታል፡፡
አሜሪካ በባልቲሞር የሚገኘው ፍራንሲስ ስኮት ኪይ የተሰኘው ታዋቂ ድልድያ ላይ ያጋጠማት አደጋ ሌላኛው የመገናኛ ብዙሀን ገዳሚ ገፅን የተቆጣጠረ ክስተት ነበር፡፡

አሜሪካ በባልቲሞር የሚገኘው ፍራንሲስ ስኮት ኪይ የተሰኘው ታዋቂ ድልድያ ላይ ያጋጠማት አደጋ ሌላኛው የመገናኛ ብዙሀን ገዳሚ ገፅን የተቆጣጠረ ክስተት ነበር፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ በባልቲሞር የሚገኘው ፍራንሲስ ስኮት ኪይ የተሰኘው ታዋቂ ድልድያይ ወደስሪላንካ ሲያቀና በነበር መርከብ ተገጭቶ በከፊል የመፍረስ አደጋ አጋጥሞታል፡፡
መርከቡ 2.6 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ድልድይ ምሰሶ ገጭቶ የተወሰነው የድልድዩ ክፍል ፈርሷል፡፡ በወቅቱ መንገዱ ላይ የነበሩ በርካታ ተሸከርካሪዎችና ስድስት ሰዎች ውሃው ውስጥ ሰምጠዋል፡፡ መርከቧም በእሳት ጋይታለች፡፡ ሁለት ሰዎችን ወዲያውኑ ከውሃው ውስጥ ማውጣት ቢቻልም ስድስት ሰዎች እስካሁን አልተገኙም ተብሏል፡፡ አስክሬን የማፈላለጉ ስራ እንደቀጠለ ነው፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአስክሬን ፍለጋና አጠቃላይ ሁኔታውን ለመመልከት ወደስፍራው እንደሚያቀኑ ገልጸዋል፡፡
ወደ አህጉረ አፍሪካ ስንመጣ ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ የደረሰው የመኪና አደጋ የአለም አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡

ተሳፋሪዎቹ ከቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኔ ወደ ሞሪያ ከተማ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በትላንትናው ዕለት ለተከበረው የፋሲካ በዓል መንፈሳዊ አገልግሎት ሲጓዙ የነበሩ ሃይማኖተኞች ነበሩ ።
ከድልድልይ ላይ ወደ 50 ሜትር ገደል በወደቀው አውቶብስ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች የስምንት ዓመት ሴት ልጅ ብቻ እንብዛም ጉዳት ሳይደርስባት በሕይወት መገኘቷም የማይረሳ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
የአውሮፓውያንን የቀን አቆጣጠር የሚከተሉ ክርስቲያኞች የስቅለት በዓልን ዓርብ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም. ያከበሩ ሲሆን የትንሳዔ በዓልን ደግሞ እሁድ መጋቢት 22 አክብረዋል፡፡
ሌላኛው የወሩ መነጋገሪያ አፍሪካዊ ጉዳይ የሴኔጋሉ ምርጫ ነበር፡፡ ሃገሪቱ በራሷም ሆነ በአፍሪካ ታሪክ በእድሜ ትንሹን ፕሬዝዳንት መርጣለች፡፡ የ44 አመቱን ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬን ፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል መንግስት ሙስና እና ሥር የሰደደ ድህነትን ሊፈታ አልቻለም በሚል በሀገሪቱ ዜጎች የበረታ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ በተለይም የካቲት ላይ ይደረጋል ተብሎ የነበረውን ምርጫ ለማራዘም የነበረው ፍላጎት በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ አስከትሎ ነበር፡፡ በእዚህም በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በስተመጨረሻ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫውን ለማዘግየት የነበረውን እቅድ ሽሮ በተደረገው ምርጫ ፋዬ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት አለመረጋጋት በኋላ በተደረገው ምርጫ በርካቶች ድምጽ ሰጥተው 19 እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት በቀረቡበት ፋዬ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
ዓለማችን የፖለቲካውን መድረክ ጨምሮ እነኚህንና ሌሎች በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳ አልፋለች፡፡ ያልተቋጩና ወደእዚህኛው ወር የተሻገሩም በርካታ ናቸው፡፡












