።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ቀጠና አካባቢው ስላላት ወቅታዊና ቀጠናዊ ሁኔታ በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርሐ ግብር ላይ በተካሄደው ሰፊ ውይይት ሀሳባቸውን የሰጡት አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር) ፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ባይተዋር እንዳልሆነች ገልጸዋል።
በቀጠናዊ ጉዳይ ዙሪያ በተደረገው ውይይት የመካከለኛው ምስራቅና ኤዢያ ፓስፊክ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አንተነህ ጌታቸው እና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ትዕዛዙ መሐመድ ሙያዊ ትንታኔዎቻቸውን አጋርተዋል።
ዶክተር አንተነህ፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የቀውስ ብዝኃነት እንደሚታይ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ቀጠናው ከጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታው አንጻር እጅግ ዘርፈ ብዙ ስፍራ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከደህንነት አኳያ ግን ያልተረጋጋ መሆኑን አክለው አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ጫፍ ላይ የደረሰ ሽኩቻ መኖሩን አጽንኦት የሰጡት ዶክተር አንተነህ አያይዘውም ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ባይተዋር እንዳልሆነች አስምረውበታል። ኢትዮጵያውያን ከቀይ ባህር ጋር ጥልቅ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ ትውስታዎች እንዳሏቸው በማስታወስ፣ ሀገሪቱ የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ይህ የባህር በር ጥያቄ ሲመለስ ከሚገኘው የልማትና የኢኮኖሚ ትሩፋት ጎረቤት ሀገራትም ተቋዳሽ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

የኤንቢሲ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርሐ ግብር ተባባሪ አዘጋጅ አቶ ትዕዛዙ መሐመድ በበኩላቸው፣ ቀጠናዊ ተጽዕኖዎችን በተመለከተ ባነሱት ሀሳብ፣ ግብፅ ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብትና የፖለቲካ አቅም ልክ ከፍ እንዳትል እንቅፋት ለመሆን እንደምትጥር ተናግረዋል።
ግብፅ ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የምትቆመው የአባይን ውሃ በብቸኝነት የመያዝና በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ሀያል ሀገር ሆኖ የመውጣት ቅዠት ስላላት መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን የባህር በር የይገባኛል ጥያቄ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ የሚያስረዱና እውነታውን የሚያረጋግጡ ጠንካራ የሚዲያ ትርክቶች እንደሚያስፈልጉ ያነሱት ዶክተር አንተነህ የሚዲያ ተቋማትና ምሁራን የሀገሪቱን ፍትሃዊ ጥያቄ በተደራጀ መልኩ በማቅረብ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውሰዋል።
በሳምንት ሁለት ጊዜ በሚቀርበው፣ዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ጉዳዮችን በሚዳስሰው “ኤንቢሲ ዓለም አቀፍ” ፕሮግራም ላይ ምሁራኑ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ውይይት አድርገዋል።
በ -ታደለ ገበየሁ
። ። ።
ማስፈንጠሪያውን (ሊንኩን) በመጫን NBC ኢትዮጵያን ይጎብኙ ይወዳጁ
https://linktr.ee/NBCEthiopiaTV
#NBCEthiopia
#ሆኖ_መገኘት
#Ethiopia












