
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የከተማዋንና የሀገሪቱን የቱሪዝም እድገት ለማሳደግ በርካታ አዳዲስና ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የቢሮው የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ እንደገለጹት፤ ተቋማቸው አዲስ አበባን በቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅ በርካታ ርቀቶችን እየተጓዘ ይገኛል።

ይህንንም ለማሳካት በከተማዋ ትልልቅ ኮንፈረንሶች እንዲካሄዱ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም አዲስ አበባን ይጎብኙ (Visit Addis Ababa) የመሳሰሉ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የማስተዋወቅ ሁነቶችን በስፋት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ከእነዚህ ጥረቶች መካከልም ኢትዮጵያ በቱሪዝም እና በኮንፈረንስ ዘርፍ ከፍተኛ ስም ባለው
የIMEX 2026 ዓለም አቀፍ ሁነት ላይ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ መሆኗ የሚጠቀስ ነው ሲሉ አቶ ሁንዴ ገልፀዋል ።
በመድረኩ ላይ በርካታ የሀገሪቱን ገጽታ የሚያጎሉ የማስተዋወቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል ።
እንደ ሃላፊው ገለፃ በ2018 ዓ.ም ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ከ220 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶች በስኬት የተካሄዱ ሲሆን፣ ይህም ከተማዋ ለዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ያላትን ተመራጭነት በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።
ለኮንፈረንስ ምቹ የሆኑ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው የከተማዋን የቱሪዝም ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል ያሉት ሀላፊው ፣በተለይም እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ እና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ያሉ ዘመናዊና ሁለገብ ስፍራዎች የብዙ አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ሁነቶን መሳብ እንደቻሉም ተናግረዋል ።
እነዚህ ሁነቶች ከተማዋን ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት የእርስ በእርስ የቱሪዝም እንቅስቃሴያቸውንና ፍሰታቸውን እንዲረዱና ልምድ እንዲለዋወጡ ትልቅ እድል ፈጥረዋል ነው ያሉት ።
አቶ ሁንዴ አክለውም ይህ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መነቃቃት ቀደም ሲል በከተማ አስተዳደሩ ያልተለመደ አዲስ አሰራር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ውጤታማነቱ ተረጋገጦ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ።
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ አጀንዳ ፕሮግራም ላይ ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ሀላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ ፣ከተማዋ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ተንተርሳ፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE Tourism) ዋነኛ መዳረሻ ለማድረግ የምታደርገውን የለውጥ ጉዞ አጠናክራ የምትቀጥል ይሆናል ሲሉ የተናገሩት ።
በ ታደለ ገበየሁ












