ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራችው ቆይታ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት በህወሃት ጦርነት ናፋቂነት መክሸፉን ገለጹ፡፡
በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልእክት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በመጠበቅ፣ በመላ አገሪቱ “አንድ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት” ብቻ እንዲኖር ማድረግ እና የታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት የመመለስ ሂደት መዘርጋት፥ አልፎም በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩትን መሰረተ ልማቶች ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ማድረግ የፕሪቶሪያ ስምምነት ነበር ብለዋል፡፡
አክለውም ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦቶችን ያለ ምንም ገደብ እንዲደርሱ ማስቻል እና በጦርነቱ ምክንያት ክመኖሪያችው የተፈናቀሉትን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት ለሰላም ሂደቱ መሳካት የራሱን ድርሻ ቢወጣም በሕወሓት በኩል ግን ስምምነቱ የሚጠይቃቸውን ግዴታዎች ከመፈጸም ይልቅ ወደ አዲስ የጦርነት ዝግጅት እና ወጣቶችን በግዴታ ወደ ማፈስ ገብተዋል። ይህም ስምምነቱ እንዲጥስ አድርጎታል፡፡
የስምምነቱን መሠረታዊ ህጎች በመጣስ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ተደርገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፌዴራል መንግሥት ብቸኛ ድርሻ የሆኑትን የአየር መንገድ እና የባንክ አገልግሎቶችን የማደናቀፍ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰዋል።
መንግሥት አሁንም በሰላም መንገድ ችግሮች እንዲፈቱና ከጥፋት አቅጣጫ እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ምክርና ማሳሰቢያ ቢሰጥም ጥሪውን ባለመቀበል ከተለያዩ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመሻረክ አዲስ ጦርነት ታውጇል ብለዋል። ይህ አካሄድ ደግሞ በይፋ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከሽፍ እና ሂደቱ ወደነበረበት የፖለቲካ እና የደህንነት ስጋት እንዲመለስ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመ የሰላም ስምምነት ነው፡፡
በ-የአብስራ ተፈራ













