
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቶፓን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የውጭ መንገደኞች መውጫ ስፍራ ላይ ቨርቹዋል የቱሪስት መረጃ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ወጪ በሁለቱ ተቋማት የሚሸፈን ሲሆን፤ ማዕከሉ እንግዶች በሚሳፈሩበት አቅራቢያ እንዲገነባ ታቅዷል። ይህ የቨርቹዋል ማዕከል በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ባለው አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም እንደሚካተት ተገልጿል።
ግንባታውን የሚያከናውነው ቶፓን ኢትዮጵያ ሲሆን፣ የጋራ መግባቢያ ሰነዱን የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ስለሺ ግርማ እና የቶፓን ኢትዮጵያ ተወካይ ወ/ት ቃልኪዳን አረጋ ተፈራርመውታል። ሚኒስትር ዴታው ከቶፓን ግሩፕ ምክትል ፕሬዘዳንት አንቶንዮ ታንጉን ጋርም ውይይት አድርገዋል::












