ልክ በዛሬዋ ቀን እ.ኤ.አ ነሀሴ 29 1958 ማይክል ጆሴፍ ጃክሰን (ማይክል ጃክሰን) አሜሪካ ውስጥ በጋሪ ኢንዲያና ግዛት ተወለደ።
አባቱ ጆ ጃክሰን ጊታሪስት የነበረ ቢሆንም ከማይክል እናት ካትሪን ጃክሰን ጋር ጋብቻውን ተከትሎ የሙዚቃ ፍላጎቱን ለመተው ቢገደድም በልጁ ማይክል ጃክሰን ማካካስ ችሎል፡፡
ማይክል በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በዓለም ላይ በጣም ታዋቂ እና ተደማጭነትን ካገኙ ዘፋኞች መካከል አንዱ የሆነ አሜሪካዊ ዘፋኝ እና ዳንሰኛ ነበር።
በዚህም በ1980ዎቹ የነበሩ ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ወደ እራሱ ስልቶች ለውጦ “የፖፕ ንጉሥ” የሚል ስያሜ አግኝቷል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃኖች በዘር ተከፋፍለው በነበረበት እና አፍሪካ አሜሪካዊያን አርቲስቶች የዕይታ ሰዓታትን ለማግኘት ሲቸገሩ የነበረውን መጥፎ ጊዜ መቀየር መቻሉም ይነገርለታል፡፡ የጥቁር ዘፋኞችንና ሙዚቀኞች የመብት ተሞጋች የሚለውን ማዕረግም ተሰጥቶት ነበር፡፡
ማይክል ብዙ አልበሞችን ለአድማጮቹ ያደረሰ ሲሆን ከነዛም መካከል “Music and me”፣ “ Ben”፣ “ off the wall”፣ “ Invincible “ ተጠቃሽ ናቸው።
ማይክል በኢትዮጵያ ያጋጠመውን ድርቅ ተከትሎ የተፈጠረውን ረሃብ ለማገዝ በተዘጋጀው “WE ARE THE WORLD” የሙዚቃ ፕሮግራም ላይ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ተሳትፎ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዲሰበሰብ አስተዋጽኦ አድርጎል፤ በዚህ ተግባሩም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር ችሎ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 25 2009 በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ በ50 ዓመቱ ህይወቱ አልፎል፡፡
በ-ሔርሜላ ተመስገን












