አርቲስት ደበበ እሸቱ ባለፉት ስድስት አስርት አመታት በላይ በተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎች ሀገሩንና ህዝብ ሲያገለግል ቆይቷል።
የበርካታ ጥምር ሞያዎች ባለቤት ደበበ እሸቱ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ እሁድ ነሀሴ 11/2017 ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል። በዛሬው እለትም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ከፍተኛ የመንግስት አካላት፣ ቤተሰቦቹና የሞያ አጋሮቹ በተገኙበት ግብአተ መሬቱ ተፈፅሟል።
ሁለገቡ አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1933 ነው የተወለደው፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከ1943- 1950 ዓ.ም ተከታትሏል።
በ1950-1951 በኢትዮጵያ አየር ሀይል ፓይለት ማሰልጠኛ ተቋም ገብቶ ሰልጥኗል። ከ1951 እስከ 1953 ዓ.ም በደብረብርሃን መምህራን ኮሌጅ ትምህርቱን ተከታትሎ ትውልድን የማነፅ ስራንም ሰርቷል።
በ1953 ተቃዋሚዎችን ደግፈሀል ተብሎ በጎሬ በእስር እዳሳለፈ የታሪክ መዝገቡ ያስረዳል። ከ1956 በያኔው ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርስቲ በመግባት የክዋኔ ጥበባት ሀሁን ቆጥሯል። በ1958 ከፍ ላለ የስነ ጥበብ ትምህርት ከመጀመሪያዎቹ ጥቁር ተማሪዎች አንዱ በመሆን ሃንጋሪ ቡዳፔስት በመሄድ ከኢትቩሽ ሎራንድ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተመርቋል።
ከውጭ ሀገራት በቀሰመው ትምህርት ከሌላኛው ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የቲያትር እድገት ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ተጫውተዋል። አርቲስት ደበበ እሸቱ ከሰራቸው አያሌ የመድረክ ስራዎች ያላቻ ጋብቻ፣ ጠያቂ፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ የቬኑሱ ነጋዴ ፣ ሼክስፒር ይጠቀሳሉ።
ዘ ሴለር ፍሮም ጂብራልተር፣ ሻፍት ኢን አፍሪካ ፣ ጉማ፣ አፍሪካ ፣ ሬድ ሊቭስ፣ ዜልዳ ደግሞ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከተሳተፉባቸው አለም አቀፍ ፊልሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
አርቲስት ደበበ እሸቱ በፈረንጆቹ 1985 ዚምባቡዌ በተካሄደው ቴአትር ለልማትና ዕድገት ወርክሾፕ ላይ በብቃት በመሳተፍ የአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ማሕበርን አስተባብረው በማቋቋም የማሕበሩም መስራች ፕሬዚዳንት ሆነው ለ12 ዓመታት አገልግሎል፡፡
ለአፍሪካ ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ወስዶል። ጣይቱ ኢንተርቴንመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቲያትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ በአትላንታ ጂኦርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለዓለም ቲያትር ባደረገው አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24ን የደበበ እሸቱ ቀን በሚል ሰይሞታል፡፡
የኢትዮጲያ ባህል ሚኒስትርም ለኢትዮጲያ ፊልም እድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ ሸልሞታል፡፡ በጉማ አዋርድም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኖል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2015 በቫንኮቨር ዓለማቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ተሸላሚ ሆኖል፡፡ በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሃገሩ ላበረከተው አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሸልሞታል።
አንጋፉው አርቲስት ደበበ እሸቱ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ አርፎል። በዛሬው እለትም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ግብአተ መሬቱ ተፈፅሟል። አርቲስት ደበበ እሸቱ የ3 ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንዲሁም የ8 የልጅ ልጆች አያት ነበር።
በ-የአብስራ ሚሊዮን












