ለ2018 የትምህርት ዘመን የሚያስፈልጉ የመማሪያ መጽሐፍት ሥርጭትን ጨምሮ የደብተር እና የተማሪዎች የደንብ ልብስ ለማሰራጨት ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች መጽሐፍት ጥምርታን አንድ ለአንድ ማዳረስ የሚያስችል በቂ መጽሐፍት ታትመው ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች እየተሰራጩ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ለግል ትምህርት ቤቶችም በቂ የመማሪያ መጽሐፍት ታትመው ለግዢ መቅረባቸውን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሳምሶን መለሰ ለኢዜአ አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል በ21 የጨርቃርቅ ፋብሪካዎች(ጋርመንቶች) የተማሪዎች የደንብ ልብስ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሥር ከሥር ለትምህርት ቤቶች የማስረከብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ለተማሪዎች የሚሆን የደብተር አቅርቦትን በተመለከተ ቢሮው ለክፍለ ከተማ ማስረከቡንና በዚህ ሳምንት ለትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ሥራ ይጀመራል ነው ያሉት፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከ2017 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት ዓይነቶች የተማሪ-መጽሐፍት ጥመርታ 1 ለ 1 መደረጉንም ነው ያስታወቁት፡፡












