ኢራን ከአሜሪካ ዋስትና ሳታገኝ ወደ ኑክሌር ድርድር እንደማትመለስ አስታወቀች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ ቴህራን በኑክሌር መርሃ ግብሯ ላይ ድርድር ለመቀጠል ከዩናይትድ ስቴትስ ጊዜና ዋስትና እንደሚያስፈልጋት አስታውቀዋል ።
አራግቺ ይሄን ያሉት እስራኤል የኢራንን የኑክሌር መርሃ ግብር ለማፍረስ በማለም ለ12 ቀናት ስታካሂድ የቆየችው ጥቃት እልባት ካገኘ በኋላ ነው። ሚኒስትሩ የእስራኤል ዘመቻ ግቡን እንዳላሳካ ተናግረው ፣ ኢራን በቅርቡ ዩራኒየም ማበልጸግ እንደምትጀምር እና “የባከነውን ጊዜ እንደምታካካስ” አጽንኦት ሰጥተዋል።
አራግቺ፣ አሜሪካ በድርድሩ ወቅት ወታደራዊ ጥቃት እንደማትሰነዝር እስካላረጋገጠች ድረስ ድርድሩ በፍጥነት እንደማይጀመር ገልጸዋል። “ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አሁንም ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገናል” ሲሉም አክለዋል።
ኢራን በቅርቡ በኑክሌር ተቋሞቿ ላይ በርካታ ጥቃቶች ቢሰነዘሩም የኑክሌር መርሃ ግብሯ ሰላማዊ እንደሆነ ደጋግማ ገልጻለች። ይሁን እንጂ፣ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ጥቃቶቹን አላወገዘም ስትል ከድርጅቱ ጋር የነበራትን ትብብር ማቋረጧን ማስታወቋ ይታወሳል።
ዘገባው የ ዘ ታይም ኦፍ እስራኤል ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












