June 28, 2025
በዛሬው ዕለት ተማሪዎቻቸውን እያስመርቁ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል፤ የአዲስ አበባ እና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይገኙበታል።
ለ75 ዓመታት በሰጠው አበርክቶ ከ280 ሺህ በላይ ተመራቂዎችን ያስመረቀ የአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ፣ 3 ሺህ 334 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 2 ሺህ 859 በሁለተኛ ዲግሪ፣ 304 በሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም 352 የስፕሻሊቲ እና ሰብ-ስፔሻሊቲ በአጠቃላይ 6849 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ “ተመራቂዎች በሥራ ሂደታቸው ለችግሮች ተጠያቂ ከመፈለግ ይልቅ ችግር ፈቺ መሆን አለባቸው” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ ጌታቸው ረዳ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና በርካታ ጥሪ የተደረገላቸ እንግዶች ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ 1 ሺህ 554 ተማሪዎችን እያስመረቀ የሚገኘው የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት መርሃ ግብሩን እያከናወነ ይገኛል። ለ17ኛ ጊዜ ተማሪዎቹን እያስመረቀ ሲሆን፣ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በርቀት እና በማታው መርሃ ግብር እያስተማርተ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በሽር አብዱላሂ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ሌላው በዛሬው ዕለት ሰልጣኞቹን ያስመረቀው እና ላለፉት 11 ዓመታት ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ 57 ወንድ እና 43 ሴት ስፖርተኞችን አስመርቋል።













