የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የጎብኚዎች ፍሰት ለማሳደግ፣ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎችን ክህሎት ማሳደግና የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማዘመን ወሳኝ ሚና እንዳለው በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩት የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አሸናፊ ስለሺ ገለፁ።

ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት፤ አንድ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያ ስኬታማ እንዲሆን ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ሊያሟላ ይገባል ያሉ ሲሆን ይኸውም ጥልቅ የሆነ እውቀትና ሙያዊ ክህሎት ናቸው ብለዋል ።
ከዚህ በተጨማሪም አስጎብኚዎች መልካም ስብዕና የተላበሱ፣ ሙያቸውን በፍቅር የሚወዱና የጎብኚዎችን ፍላጎት በሚገባ መረዳት የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በቅድሚያ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በሚገባ መለየትና ምን አይነት ስራዎች ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል መረዳት ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህንን እውን ለማድረግም በሁሉም የቱሪዝም ዘርፎች ላይ የሰለጠነና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት የግድ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አሸናፊ ይህንን ማሻሻል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም የዲጂታል አማራጮችን በስፋት በመጠቀም የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋወቅና የጎብኚዎችን ፍሰት ማሳደግ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በቀጣይ የምታስተናግደውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) አስመልክቶም ሰፊ ሀሳብ ተነስቷል።
ጉባኤው ለሀገሪቱ ትልቅ የቱሪዝምና የገጽታ ግንባታ እድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን በመረዳት፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም ከጉባኤው ጋር ተያይዞ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድና የተፈጠሩትን መልካም አጋጣሚዎች ወደ ገበያ ለመቀየር የሚያስችሉ የተቀናጁ ስራዎች ለመስራት መታሰቡም በመድረኩ ላይ ተመላክቷል።
በ ታደለ ገበየሁ



