ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩ በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ በተካሄደው 8ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ላይ ተገለጸ።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደቱ ዋና ተደራዳሪ ያስሚን ወሀብረቢ የተመራው የልዑካን ቡድን ስብሰባውን ጀምሯል።
ሚኒስትሯ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳስገነዘቡት፣ የድርጅቱ አባልነት ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል ሲሆን፣ የቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት አንዱ ነው።
የሀገራችን የድርጅቱ አባል መሆን የፖሊሲ ቀጣይነትን እና ግልጸኝነትን ከማጠናከሩም በላይ፣ ምርትና ምርታማነትን፣ የውጭ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን በማስፋት የሥራ ዕድልን ለመፍጠር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው።
ከባለብዙ ወገን ስብሰባው ጎን ለጎን፣ የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ተካሂዷል። ከሁለቱም ወገኖች ጋር የተካሄደው ድርድር እጅግ ፍሬያማ ነበር። እስካሁን ለሁለትዮሽ ድርድር የጠየቁ 17 ሀገራት ሲሆኑ፣ ከ11 ሀገራት ጋር ስምምነት ተፈርሟል።
የድርድር ቡድኑ ቀሪ ባለብዙ ወገን የእንጥልጥል ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ የተገኘውን ፍጥነት ለመጠበቅ እና ድርድሮችን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ተሳካ መደምደሚያ ለማድረስ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት፣ የጋራ ኃላፊነት እና በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የቀጠለ ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
8ኛው ዙር ድርድር እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 9-10 ቀን 2026 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በጄኔቫ እየተካሄደ ይገኛል።
















