May 23፣ 2026
NBC Ethiopia
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካን መርቀዋል።

በግራንዴር ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገነባው ፋብሪካ፣ መሰረት ልማቱ በ300,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የሴራሚክና የፖርሲሌን ንጣፎች ማምረቻ ፋብሪካ ሲሆን፤ ከዕቅድና መሬት ዝግጅት እስከ ሙሉ ሥራ ማስጀመር የወሰደው ጊዜ ዘጠኝ ወራት ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት 60×60 የሴራሚክ ንጣፎችን በስፋት ማምረት የጀመረው ይህ ፋብሪካ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የምርት ዓይነቶቹን በማስፋት የ80×80፣ 60×120፣ 70×140 እና 80×160 መጠን ያላቸውን የንጣፍ ዓይነቶች እንዲሁም የአውሮፓን የጥራት ደረጃ ያሟሉ የፖርሲሌን ምርቶችን ማቅረብ እንደሚጀምር ይጠበቃል። ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ-ነዋይ የወጣበት ይህ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያመላከተ ክንውን ነው።

ለፋብሪካው ምርት የሚያስፈልጉት ጥሬ ዕቃዎች 80 በመቶ የሚሆነው ከፋብሪካው በ100 ኪሎ ሜትር ክበብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ይህም ሙሉ በሙሉ የተቀናጀና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተሳሰረ የአቅርቦት ሰንሰለት ፈጥሯል። ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ባሳለፍናቸው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ4.85 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን በቻለችበት በዚህ ወቅት፤ የግራንዴር ሴራሚክ መከፈት የውጭ ምርት ጥገኝነትን የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላትም ጭምር ነው።












